ዜናፖለቲካ

ዜና፡ አምነስቲ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት የሰየመው የአለም አቀፉ መርማሪ ቡድን በኢትዮጵያ የስራ ግዜ እንዲራዘም ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2016 ዓ.ም፡- አምነስቲ ኢንተርናሽናል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን እንዲመረምር ያቋቋመውን የባለሞያዎች ቡድን የምርመራ ግዜ እንዲያራዝም መስከረም 7 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ጠይቋል።

አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ተቋም አምነስቲ ባወጣው መግለጫ አሁንም በሀገሪቱ ቀውሶች እየተስፋፉ ይገኛሉ ሲል ገልጿል። የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብት ምክር ቤት አባል ሀገራት የአለም አቀፉን የመርማሪዎች ቡድን የስራ ግዜ በማራዘም በሀገሪቱ ላይ አለምአቀፍ ትኩረት እንዲደረግ ማስቻል አለበት ሲል ጠይቋል።

አጣሪ ቡድኑ ይፋ ያደረገው ሪፖርት በሀገሪቱ ከግጭቶች ጋር የተያያዘ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምንኛ እንደከፋ ያሳያል ያለው አምነስቲ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተለይም በትግራይ የነበረው የሰብአዊ መብት ጥሰት ወደ አማራ እና ኦሮምያ ክልሎችም እየተስፋፋ መሆኑን ያሳያል ብሏል።

የመርማሪ ቡድኑ ሪፖርት የሚያሳየው የመንግስታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን ምርመራ ለማቆም ግዜው አሁን አለመሆኑን ነው፣ ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ አለበት ሲሉ የተቋሙ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዳይሬክተር የሆኑት ቲገረ ቻጉታህ መናገራቸውን ያካተተው መግለጫው በአማራ ክልል እየተካሄደው ያለው ግጭት እና እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ሀገሪቱ አደገኛ አፋፍ ላይ መሆኗን ያሳያል ማለታቸውን አስታውቋል።

የመርማሪ ቡድኑ ተወደፊት  እጣፈንታ በመካሄድ ላይ ባለው የምክር ቤቱ 54ኛ ጉባኤ ላይ ይወሰናል።

በኢትዮጵያ የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደቀጠለ ነው ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለሞያዎች ቡድን ትላንት መስከረም 7 ቀን 2015 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

በፌደራል መንግስቱ እና በትግራይ ሀይሎች መካከል የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ከአንድ አመት በኋላ የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ኤክስፐርቶች በኢትዮጵያ (ICHREE) ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረበው ሪፖርት በኢትዮጵያ አሁንም የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸም ወንጀል እንደቀጠለ ነው፤ በሀገሪቱ ሰላም ሰፍኗል ለማለት አስቸጋሪ ነው ሲል መግለጹም በዘገባው ተካቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በአማራ ክልል የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ከታወጀ ወዲሀ ደግሞ በርካታ ግፎች በንጹሃን ላይ መፈጸሙን አስታውቋል። ቢያንስ አንድ የድሮን ጥቃት በፌደራል መንግስቱ ተፈጽሟል ብሏል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የትላንቱን መግለጫ በተናጠል ከማውጣቱ ቀደም ብሎ በአለማችን ከፍተኛ ተጽኖ ፈጣሪ የሆኑ ታላላቅ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ በመሆን የመንግስታቱ ድርጅት በኢትዮጵያ የሚያካሂደውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲመረምር ያቋቋመውን ቡድን ተልዕኮን ለተጨማሪ አንድ አመት እንዲያራዝም መጠየቃቸውን የተመለከተ ዘገባ ማቅረባችን ይታወሳል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ካውንስል ከሚያካሂደው 54ኛ ጉባኤውን በፊት ጳጉሜን 2 ቀን 2015 ዓ.ም አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይት ዎች፣ ኦክስፋም እና የአለም የሰላም ፋውንዴሽንን ጨምሮ 63 የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጋራ በጻፉት ደብዳቤ በኢትዮጵያ በከፋ ሁኔታ እየተፈጸመ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መርማሪ ቡድን በተጨማሪ ለአንድ አመት በማስቀጠል ምርመራ ሊካሄድበት ይገባል ብለዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button