ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ በጋምቤላ ክልል በዘጠኝ ወረዳዎች በተከሰተው የውሃ መጥለቅለቅ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቀሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8/2016 ዓ.ም፡– በጋምቤላ ክልል ጋምቤላ ከተማን ጨምሮ በዘጠኝ ወረዳዎች ወንዞች ሞልተው ባስከተሉት የውሃ መጥለቅለቅ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውንና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ መንግስት አስታወቀ

በክልሉ ደጋማው አካባቢ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት በኑዌር ዞን የሚገኙ አምስቱም ወረዳዎች ማለትም ኢታንግ ልዩ ወረዳ፣ ጋምቤላ ወረዳ፣ ጎግና ጆር ወረዳዎች ላይ የውሃ መጥለቅለቅ መከሰቱንና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይና የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ኡሞድ ኡሞድ ተናግረዋል።

አቶ ኡሞድ ኡሞድ እንዳሉት የክልሉ አብዛኛው ህዝብ አሰፋፈር ወንዞችን የተከተለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባሮ፣ የአልዌሮ፣ የጊሎና የአኮቦ ወንዞች ሞልተው በመፍሰስ በአቅራቢያው የሚኖሩ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል ብለዋል።

በጋምቤላ ከተማ በ01፣ 02፣ 04 እና 05 ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች በውሃ ሙላት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው አከባቢዎች ሲሆኑ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች የቤት እንስሳቶችና ሌሎች ንብረቶች ሙሉ በሙሉ በውሃ በመወሰዳቸው ሜዳ ላይ ወድቀናል ሲሉ ተናግረዋል።

አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሚገኘው የባሮ ወንዝ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል የሚሉት ነዋሪዎቹ መንግስት ሊመለከታቸውና ጊዚያዊና ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊያበጅላቸው እንደሚገባ ገልፀዋል።

አቶ ኡሞድ የውሃ መጥለቅለቅ ከደረሰባቸው ወረዳዎች፤ ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ጠቅሰው ተፈናቃዮቹን ለጊዜው ደረቃማ በሆኑ አካባቢዎች እንዲጠለሉ ተደርጓል ብለዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ለማድረግ የአደጋውን መጠን የመለየት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሰሠራ እንደሆነም ገልፀዋል።

በቀጣይም የወንዞቹ ሙላት ሊጨምርና ከዚህ የከፋ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የገለፁት አቶ ኡሞድ ህብረተሰቡ ይህንን አውቆ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል። አቶ ኡሞድ አክለውም በጎርፍ አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ ተወካይና የጤና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሳይመን ቲያች የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑ ገልፀው የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ ነዋሪዎችን የመለየት ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይም መንግስት ጉዳት የደረሰባቸውን ወደ አንድ ስፍራ ለመውሰድና የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የከተማው አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ክላኝ ቱት በበኩላቸው ተጎጂዎችን ወደ ደረቃማ ስፍራ ለመውሰድ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙና መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጠማሪ መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችም የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፏል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button