ዜናህግ እና ፍትህ

ዜና፡ በጋምቤላ ክልል በህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች ቆሰሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19/ 2016 ዓ/ም፡_ በጋምቤላ ክልል ትላንት መጋቢት 18፣ 2016 ዓ/ም ከጋምቤላ ከተማ ወደ ኑዌር ዞን ላሬ ወረዳ በመጓዝ ላይ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት የሶስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

በርካታ ምንጮች ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጹት፤ ጥቃቱ የተፈፀመው በአቦል ወረዳ እና በታርፋም ከተማ መካከል ትላንት ጠዋት 4፡00 ሰዓት አካባቢ አውቶቡሱ እየተጓዘ በነበረበት ወቅት 10 ሰዓት አካባቢ ነው።

አንድ ምንጭ እንደገለጸው፤ ትላንት ጠዋት በርካታ አውቶቢሶች ከጋምቤላ ከተማ በጠዋት በመውጣት ሲጓዙ ነበር። ነገር ግን አንድ አውቶቢስ ዘግይቶ በመውጣቱ በታጣቂዎቹ ጥቃት ሊደርስበት ችሏል።

“ጥቃት አድራሾቹ፤ ኢላማ ያደረጉት ሁሉንም አውቶቢሶች ነው። አንደኛው ዘግይቶ በመውጣቱ ለጥቃቱ ተጋልጧል” ሲል ገልጿል። 

ሌላኛው ነዋሪ፤ በጥቃቱ አንድ ህጻንን ጨምሮ አሽከርካሪውና አንድ ሴት ህይወታቸው አልፏል ሲል ገልጿል። አክሎም፤ ጥቃቱን የፈጸሙት “የአኙዋ” ታጣቂዎች ቡድን ናቸው ብሏል።

ከዚህ በተጨማሪም፤ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ከጋምቤላ ከተማ በ50 ኪ/ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አቦቦ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት አምስት ሰዎች መገደለቸውን ምንጩ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። 

በግንቦት ወር 2015 ዓ/ም በጋምቤላ ክልል በኢታንግ ልዩ ወረዳ እና በጋምቤላ ከተማ በተከሰተ የእርስ በርስ ግጭት የዘጠኝ ሰው ህይወት ማለፉንና 17 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል መድረሱን ተከትሎ በክልሉ ተደጋጋሚ ጥቃቶች እየተፈጸመ ይገኛል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በክልሉ ጥር 13፣ 2016 ከላሬ ወረዳ ወደ ጋምቤላ እየተጓዘ ባለ የህዝብ ማመላለሻ ባስ ላይ ኢታንግ እና አቦል መካከል በተፈፀመ ጥቃት በተወሰኑ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

በተጨማሪም፤ አዲስ ስታንዳርድ በክልሉ ማጃንጋ ዞን ስር በምትገኘው ጎደሬ ወረዳ ነሃሴ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ምሽት ላይ ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት ስድስት የወረዳዋ ነዋሪዎች ህይወት ማለፉን ዘግቧል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button