ዜናፖለቲካ

ዜና: የጋምቤላ ክልል መንግስት “በክልሉ ስልጣንን በኃይል ለመንጠቅ” በሚያስቡ ላይ የማያዳግም እርምጃ እወስዳለሁ ሲል አስጠነቀቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21/2016 ዓ.ም፡- የጋምቤላ ክልል መንግስት ትላንት መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ በከልሉ ከ2014 ዓ.ም በኋላ ዋና ከተማዋን ጋምቤላን ጨምሮ በክልሉ አንዳንድ አካባቢ “የብሔር ግጭት፣ ሽብርተኝነት፣ ደረቅ ወንጀሎችና ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎች ዝውውር” መበራከታቸውን አመላክቷል።

“ሥልጣንን በኃይል ለመንጠቅ ኢ-ህገመንግሥታዊ አካሄዶችን” ለመጠቀም የምታስቡ ሀይሎችን አልታገስም ሲል የክልሉ መንግስት በመግለጫው አስጠንቅቋል።

ከመሬት ጋር ያሉ ጨለምተኛ አተያይ የሆኑ ነጠላ ትርክቶች በውስጣችን በሚነዙት ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰዱ ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብሏል፡፡

ከዚህም ጎን ለጎን በአባባሽነት የሚጠቀሱ ጽንፈኛ ማህበራዊ ሚዲያዎችና አንድነታችንን ጠብቀን እንዳንጓዝ የሚያደርጉን ጽንፈኛ ዳያስፖራዊያንን እንዲሁም ሌሎች ተዋናዮች በነቃ የሃሳብ ትግል ልንመክታቸው ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡

በክልሉ ውስጥም በየጊዜው የሚፈጠሩ ጫፍ የደረሰ የብሔር ጽንፈኝነት፣ የተለያየ የፖለቲካ አተያይ ችግሮች በዋናነት ተሸካሚው አመራሩ መሆኑን የጠቆመው መግለጫው በሌሎች ተዋናዮች የታጀበ ነው ሲል አትቷል፤ ለአብነትም ኢ-መደበኛ አደረጃጀት፣ ተጠያቂነት የሌላቸው ከውጪ የሚዘወሩ የማህበራዊ ሚዲያዎች ሲል ጠቅሷል።

በአመራር የነበረውን የፖለቲካ ብልሽት ለማረም በየደረጃው የሚገኘውን የከፋ ችግር ውስጥ የገቡትን አመራሮች ከነበሩበት የኃላፊነት ቦታ እንዲነሱና ተጠያቂ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ መሰራቱንም ጠቁሟል።

አሁንም ችግሩ ከመቀነስ ይልቅ እየተባባሰ እንዲሄድ የማድረግ ዝንባሌ በመኖሩ ለህዝባችን ሠላም ሲባል፤ የክልሉ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት በተፈፀሙ ወንጀሎች እጃቸው ያለበት በቁጥጥር ስር ውለው እንዲጠየቁ የማድረግ ሂደት ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሌላ በኩል በክልሉ የፀጥታ በመዋቅር ውስጥ ያለውን ችግር በዘለቄታነት በመፍታት የህዝቡን ሠላም ለማስጠበቅ ይቻል ዘንድ፤ ከፀጥታ ተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች ጀምሮ እስከ መደበኛ ፖሊሶች የደረሰ ጥልቀት ያለው ግምገማ መጀመሩን አስታውቋል።

መደበኛ ሥራዎች ሳይስተጓጎሉ በወንጀል ድርጊት እጁ ያለበት ማንኛውም አካል ላይ መንግሥት እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button