ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር “ዛቻ እየሰነዘረብኝ፣ ጠብ እያጫረብኝ” ነው ሲል ገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19/2016 ዓ.ም፡- የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ባወጣው መግለጫ “የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ መጋቢት 16 ቀን 2016 ዓ/ም የአማራ ክልል ተማሪዎች መማሪያ መጻህፍትን እንደሰበብ ተመርኩዞ ያወጣውን የዛቻ እና የጠብ አጫሪነት መግለጫ ተመልክተናል” ሲል አስታውቋል፡፡

ጊዚያዊ አስተዳደሩ ያወጣው መግለጫ በተሳሳተ ካርታ ወደ አማራ ክልል ተካተዋል ያላቸውን አካባቢ ሕዝቦች “ታሪካዊ እውነታን፣ ተጨባጭ ማስረጃዎችን እና ነባራዊ ሐቅን የካደ” ነው ሲል የተቸው የአማራ ክልል መግለጫ “አሳሳችና የጠብ አጫሪነት ፍላጎትን የተሸከመ” ነው ሲል አመላክቷል።

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ ባወጣው መግለጫው በትናንትናው እለት ማለትም መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ደግሞ ከነበረበት አካባቢ በመንቀሳቀስ የራያ አላማጣ ወረዳ ቀበሌዎችን በመያዝ “ነዋሪዎችን በመግደልና በማሰቃየት ላይ ይገኛል” ሲል ኮንኗል፡፡

በራያ በኩል ስለተፈጠረው ሁኔታ የጠየቅናቸው በአማራ ክልል መንግስት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ሁነው የተሾሙት ሀይሉ አበራ በአላማጣ ዙሪያ በምትገኘው ጨጓራ በተባለች ቀበሌ የትግራይ ታጣቂዎች ሰኞ ለሌሊት ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ ወደ ሌሎች አከባቢዎች ተዛምቷል ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። የትግራይ ሀይሎች የፈጸሙት ተግባር የፕሪቶርያውን ስምምነት የጣሰ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የአላማጣ ከተማ ከንቲባ ያቀረቡትን ውንጀላ በተመለከተ የጠየቅናቸው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው ረዳኢ ሀለፎም በበኩላቸው ውንጃላውን በማጣጣል “ጠቡን የጫሩት የአማራ ሀይሎች ናቸው በትግራይ ግዛት ተቀምጠው” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

“የአማራ ክልል የትግራይ ክልል ግዛቶችን አስመልክቶ የመናገር የህግም የሞራልም መሰረት የለውም” ሲሉ በመግለጽ ጉዳዩን በሰላማዊ እና ህገመንግስታዊ መንገድ ለመፍታት ዝግጁ ነን ብለዋል።

በተጨማሪም ሃላፊው የአማራ ክልል የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት “የሚያውክ ተግባር እያከናወነ ነው፣ በአከባቢው ሰላም እንዳይሰፍን የሚያደርግ ጠብ አጫሪ ስራዎች እየሰራ ነው” ሲሉ ገልጸዋል። “የአሁኑን ትንኮሳ የመጀመሪያው አይደለም፣ ክልሉ (የአማራ ክልል) በትግራይ ክልል ላይ ትንኮሳ የማካሄድ ታሪክ ያለው ነው” ብለዋል። የፌደራል መንግስቱ ጣልቃ በመግባት የክልሉን ተግባር ሊያስቆም ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የአማራ ክልል መንግስት መጋቢት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው በመግለጫው የወልቃይት ጠገዴ፣ ጠለምት እንዲሁም የወፍላ ወረዳዎች እና የራያ የማንነት ጥያቄ ያለባቸው ወረዳዎች ህዝብ እንደማንኛውም የሀገሪቱ ሕዝብ ሁሉ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚነት መብቱ ሊቀለበስ የማይችል ሁኗል ብሏል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ “በአማራ ክልል ላይ ጥቃት ከመፈጸም የማይመለስ መሆኑን የሚገልጽ የጠብ አጫሪ መግለጫ ማውጣቱ ካለፉት ድርብርብ ውድቀቶች ትምህርት አለመውሰድን ከማሳየት የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም” ሲል ተችቷል፡፡

የተፈጠሩ ችግሮችን በህግ አግባብ እንዲፈታ እተደረገ ያለውን ጥረት የአማራ ክልል መንግስት የራሱን ድርሻ እየተወጣ ባለበት ሁኔታ “በህዝብ መጎሳቆልና በወጣቶች እልቂት ትምህርት አለመወሰዱና የተለመደ ትንኮሳ በማድረግ ላይ መሆኑ እጅጉን አሳዝኖናል” ብሏል፡፡

የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ለሀገሪቱ ቋሚ ቀውስ ምንጭ ከሚያደርጉት ተግባራት እንዲታቀብ ሲል ያሳሰበው የክልሉ መገለጫ ሀገራችንንና ሁለቱን ክልሎች ወደ ቀውስ ከሚያስገቡ ተግባራት በመቆጠብ “ከለመደው አጓጉል የካርታ ፖለቲካ ጨዋታ እንዲወጣ” ሲል ጠይቋል።

የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ባደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲያተኩር እንዲሁም አንድ ሀገር ለመገንባት ለሚፈለገው ዘላቂ ሠላም እና ለሕዝቦች አንድነት መጽናት በሚበጅ ሐሳብና ተግባር ላይ እንዲያተኩር እንመክራለን ብሏል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button