ዜናፖለቲካህግ እና ፍትህ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በኢትዮጵያ ዕርቅ እውን ሊሆን የሚችለው “የተጎጂዎች ቁስል ከተፈወሰ በኋላ” ብቻ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18/2016 .ም፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተ.መ.ድ.) የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽሕፈት ቤት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በሽግግር ፍትሕ ጉዳይ ላይ ከተጎጂዎችና ጉዳት ከደረሰባቸው ማኅበረሰቦች ጋር ባደረጉት ምክክር የተገኙ ግኝቶችን በተመለከተ ባለ 90 ገጽ ሪፖርት ታህሳስ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ይፋ አድርገዋል።

ይፋ በተደረገው ሪፖርትም ዕርቅ “አስፈላጊና ሊሳካ የሚችል ግብ እንደሆነ ቢታመንም፣ የተጎጂዎች ቁስል ከተፈወሰ በኋላ ብቻ እውን ሊሆን የሚችል ጉዳይ” መሆኑን ተሳታፊዎች አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል ብሏል።

ተሳታፊዎቹ አዎንታዊ አስተዋጽዖ ያላቸው “ሃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ልማዳዊ የጋራ እሴቶች” እንዲሁም “ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዐቶች” ዕርቅ ለመፍጠር የሚያስችል ዐቅም እንዳላቸውም ማስገንዘባቸውንም አመላክቷል።

ሪፖርቱ ተጠያቂነትን፣ እውነትን መፈለግ፣ ማካካሻ መስጠትን፣ ጥሰቶች እንዳይደገሙ ዋስትና መስጠትን እና ዕርቅን ማስፈን በመሳሰሉት ዋና ዋና የሽግግር ፍትሕ ክፍሎች እና ግቦች ላይ አጽንዖት በመስጠት የተሳታፊዎችን ዕይታ እና ፍላጎቶችን ማብራራቱን አስታውቋል።

ኢሰመኮ እና የተ.መ.ድ. የሰብአዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት ለ8 ወራት ያክል ሲካሄዱ የቆዩት የማኅበረሰብ ምክክሮች ባጠቃላይ 805 ሰዎች የተሳተፉበት መሆኑን የጠቆመው ሪፖርቱ እነዚህም የተጎጂዎችንና ቤተሰቦቻቸውን፣ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን፣ የአካል ጉዳተኞችን፣ ባህላዊና የሃይማኖት መሪዎችን እንዲሁም በሰብአዊ መብቶችና ሰላም ጥረት ላይ የሚሳተፉ ሀገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ማካተቱን ገልጿል።

ምክክሮቹ በአፋር፣ በአማራ፣ በሐረሪ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሊ እና በትግራይ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር መካሄዱን እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር በሀገር አቀፍ ደረጃ ተጨማሪ ምክክር መካሄዱንም አስታውቋል።

ሪፖርቱ ቀደም ሲል ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተሟላ መልኩ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አስፈላጊነትን በግልጽ የሚያመላክትና የሚያጠናክር ነው ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ተጎጂዎችና ማኅበረሰቦች የገለጹትን የፍትሕ ፍላጎት ለማሟላት፣ በኢትዮጵያ ለተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽ የሚሰጥ፣ ሁለንተናዊ አሠራርን የተከተለ፣ መጠነ ሰፊ የሽግግር ፍትሕ ሂደት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በሪፖርቱ ተካቷል።

ተሳታፊዎችም የደረሰባቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች እና በደሎች በመመስከር እና ሐሳባቸውን በማቅረብ የእውነት ፍለጋ ሂደት አካል ለመሆን ፈቃደኛነታቸውን መግለጻቸውን አስታውቋል።

የሰብአዊ መብቶች ጥሰትና በደል እንዳይደገም የሕግ እና የተቋማት ለውጦችን እና ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም ተሳታፊዎች አጽንዖት ሰጥተዋል ያለው ሪፖርቱ ይህም ሕገ-መንግሥቱን ጨምሮ ሌሎች የሕግ እና የፖሊሲ ማዕቀፎችን መመርመርና ማሻሻልን እንደሚጠይቅ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ድረስ የወሰዳቸውን ተጨባጭ አዎንታዊ እርምጃዎች በበጎ በመቀበል፣ መንግሥት በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱን በማያሻማ መልኩ እንዲያሳይ ኢሰመኮ ጥሪውን አቅርቧል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button