ዜናቢዝነስ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በኢትዮጵያ የሚታየው የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት የተፈራረምኩትን ስምምነት በድጋሚ እንዳጤነው እየገፋፋኝ ነው ስትል ኬንያ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 7/2016 ዓ.ም፡- ኬንያ ከሁለት አመት በፊት ከኢትዮጵያ ጋር ለ25 አመታት የሚቆይ በኤሌክትሪክ ሽያጭ ዙሪያ የተፈራረምኩትን ስምምነት እንደገና ላጤነው ተገድጃለሁ ስትል ገለጸች።

ለዚህም እንደምክንያትነት የጠቀሰችው በኢትዮጵያ ያለው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር እየተባባሰ በመሆኑ እና ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ስለሚገኝ ለእኔ በሚቀርበው የኤሌክትሪክ ሀይል ላይ ችግር መፍጠሩ አይቀርም በሚል ስጋት ስላደረብኝ ነው ብላለች።

የኬንያ የኢነርጂ እና ፔትሮሊየም ተቆጣጣሪ ባለስልጣን በኢትዮጵያ ያለው የኤሌክትሪክ ሀይልቅ አቅርቦት ችግር እንዳሳሰበው መግለጹን ያስታወቀው ዘኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ዘገባ ይህም በኬንያ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ላይ አደጋ የደቀነ ነው ማለቱን ጠቁሟል።

በዚህም ሳቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ሐምሌ 2014 ዓ.ም የተደረሰው ስምምነት መከለስ አለበት ሲል ማሳሰቡን አስታውቋል።

እስካሁን ስለተከሰተው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግርም ይሁን በውሉ መሰረት ስለተስማማነው አቅርቦት ማሟላት መቻልም ሆነ አለመቻል ለኬንያም ይሁን ለባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተገለጸ ነገር የለም፤ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የተፈራረምነው የኮንትራት አስገዳጅ ስምምነት ብቻ ስለሆነ ነው ሲሉ የባለስልጣኑ ዋና ሃላፊ ዳንኤል ኪፕቶ እንደገለጹለት ጋዜጣው አስነብቧል።

ምንም እንኳ ከስምምነታቸን ውጭ በሃይል መቋረጥ ሳቢያ ለሚደርስብን ጉዳት ከኢትዮጵያ በኩል ማካካሻ የሚከፈለን ቢሆንም አሁንም በሀይል አቅርቦቱ ላይ አደጋ የደቀነ ነው ሲሉ የገለጹት ሃላፊው ስምምነታችንን በመከለስ በቋሚነት ሊቀርብልን ስለሚችለው የሀይል መጠን መፈራረም አለብን፣ እስካሁን የሚቀርብልን የኤሌክትሪክ ሀይል አነስተኛ ነው ሲሉ መናገራቸውንም ጋዜጣው አካቷል።

ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር በሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም በተፈራረመችው ስምምነት መሰረት ለአምስት አመታት የሚቆይ ሲሆን በድጋሚ ለመደራደር የምትችለው ከሶስት አመታት በኋላ ብቻ መሆኑን ጋዜጣው አውስቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button