ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: በቀራንዮ ከተማ በ’መንግስት ሃይሎች’ የተፈፀመውን አሰቃቂ ግድያን ተከትሎ ነዋሪዎች በፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13/2016 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን በቀራንዮ ከተማ ከሳምንት በፊት ሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ.ም የተፈጸመውን አሰቃቂ ግድያን ተከትሎ ነዋሪዎቹ በፍርሃት ውስጥ መሆናቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ አስታወቁ፤ ግድያው የተፈጸመው በቤተክርስቲያን አቅራቢያ በሚገኝ ቦታ የመቃብር ጉድጓድ በመቆፈር ላይ በነበሩ ሰዎች ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ከግድያው በኋላ በከተማዋ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል፣ የህዝቡ ስሜትስ ስንል የጠየቅናቸው ነዋሪዎቹ “አሁንም ጭንቀት ውስጥ ነን” ምን እንደሚመጣ አናውቅም ሲሉ ገልጸው “የከተማው ድባብ ያስጠላል፣ ከተማው ቀዝቅዟል” ብለዋል።

“ህዝቡ ተስፋ የቆረጠበት ሁኔታ ነው ያለው” ያሉን የከተማዋ ነዋሪ እና የአይን እማኝ የሞቱት ሰዎች “ከፖለቲካ አለም፣ ከትግልም ነጻ የሆኑ ናቸው፤ የቤት ጭቃ በመመረግ፣ ከመኪና እቃ በማውረድ የሚተዳደሩ ናቸው፤ አንድ በግምት ከ12 እስከ 14 አመት የሚሆነው ዲያቆን ከተገደሉት መሀል ነው” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል፤ የፍርሃት ቆፈኑ አሁንም አለቀቀንም ሲሉ ገልጸዋል።

በወቅቱ ጥቃቱ በተፈጸመበት ቦታ በመድረስ አስከሬኖቹን ካነሱት ሰዎች አንዱ ነኝ ያሉን የአይን እማኙ “በተገደሉት ሰዎች አስከሬን እና በፈሰሰው ደም ተሸፍነው የተረፉ ሶስት ሰዎች መገኘታቸውን” አስታውቀዋል። የመከላከያ አባላቱ ጥይት መተኮስ ሲጀምሩ በአከባቢው የነበሩ በርካታ ሰዎች ሸሽተው መሄዳቸውን አመላክተዋል።

ስማቸው ለደህንነታቸው ሲሉ እንዳይጠቀስ የጠየቁ ስለሁኔታው ለአዲስ ስታንዳርድ ማብራሪያ የሰጡን ነዋሪ እና የአይን እማኝ “ከሞጣ ተነስተው በቀራንዮ በኩል በፓትሮል ባለስልጣናትን ይዘው በሚጓዙ ተሽከርካሪዎች ላይ የፋኖ ሀይሎች በፈጸሙት ጥቃት የተቆጡ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ አከባቢው በመምጣት ነው ግድያው የተፈጸመው” ብለዋል።

“ከ85 አመት በላይ የሚሆናቸው መነኩሴ ሞትን ተከትሎ እድርተኞች የመቃብር ጉድጓድ ሲቆፍሩ ነበር፤ የመከላከያ አባላቱ እንደመጡ መቃብር እየቆፈሩ እንደሆነ ቢነግሯቸውም ዝም ብለው እንደተኮሱባቸው በተአምር በሚባል መልኩ ከተረፉ ሁለት ሰዎች ሰምቻለሁ” ብለዋል።

“ወዲያውኑ ስድስት ሬሳ አንስተናል አንደኛው ለህክምና ቢሄድም አልተረፈም” ያሉት የአይን እማኙ ሁለት ሰዎች መቁሰላቸውንም ጠቁመዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የመከላከያ እና ሌሎች ባለስልጣናት ጥቃቱ ከተፈጸመ ከሁለት ቀናት በኋላ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም መጥተው ነበር ያሉን ነዋሪው “የመጡት ግን ህዝቡን ለማነጋገር ሳይሆን በከተማዋ የነበረ አንድ የታጠቀ ሰው አፍነው ለመውሰድ ነበር፣ አፍነው ከወሰዱት በኋላ ከከተማዋ ውጭ ገድለውታል። እርግጥ የተገደለው ታጋይ ነው፣ መሳሪያ የታጠቀ” ሲሉ ገልጸዋል።

“ከተማዋ ላይ የመንግስት መዋቅር የለም፣ ፋኖዎች የራሳቸውን አደረጃጀት ፈጥረው፣ በህዝብ የተመረጠ ግዜያዊ ግጭት አስወጋጅ ኮሚቴ የሚል ተቋቁሞ የከተማው ህዝብ በእሱ እየተመራ ነው ያለው ” ሲሉ ነዋሪው አስረድተዋል።

የከተማዋ ሌላኛው ነዋሪ እና አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገራቸው የጤና ባለሞያም ይህንን አረጋግጠዋል። በጥቃቱ ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸው ሁለቱ ነዋሪዎች በከተማዋ በሚገኝ ጤና ጣቢያ ክትትል እያደረጉ መሆናቸውን በመግለጽ ለጉዳት የሚዳርግ አይደለም ቀለል ያለው ጉዳት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ከምስራቅ ጎጃሟ ቀራንዮ በተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እሁድ ሰኔ 9 በምዕራብ ጎጃም ዞን ጃቢጠህና ወረዳ ጂጋ ከተማ በፈጸሙት ጥቃት መምህራን እና የባንክ ቤት ሠራተኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች “መረሸናቸውን” ሁለት የዐይን እማኞች እና ከተማዋን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቡት አቶ አበባው ደሳለውን ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ ዘግቧል።

“እስካሁን ስም ዝርዝራቸው እና ሥራቸው በእጃችን የደረሰ 13 ሟቾች አሉ፤ ሁለት ደግሞ የቆሰሉ ናቸው” ሲሉ ከምዕራብ ጎጃም ዞን ጂጋ ምርጫ ክልልን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ አበባው ደሳለው እንዳረጋገጡለት ቢቢሲ በዘገባው አካቷል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button