ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በተያዘው አመት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ሃይል የሚያመነጩ ተጨማሪ 5 ተርባይኖችን ለመትከል እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4/2016 .ም፡ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሃይል የሚያመነጩ ተርባይኖችን ቁጥር 7 ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) ገለጹ። በ2014 ዓ.ም ሃይል ማመንጨት ከጀመሩት ሁለት ተርባይኖች በተጨማሪ በያዝነው ዓመት 5 ተርባይኖችን ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር ኢ/ር) መናገራቸውን ፋና በዘገባው አስታውቋል።

ወደ ስራ ከገቡት ሁለት ተርባይኖች አንጻር ዘንድሮ ወደ ስራ የሚገቡት 5ቱ ተርባይኖች ሃይል መጠን የበለስ ፣የግልገል ጊቤ አንድና ሁለት እንዲሁም የተከዜ የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከሚሰጧቸው አማካይ 1 ሺህ 180 ሜጋ ዋት ተመጣጣኝ ወይም የሚበልጥ ሃይልን ያመነጫሉ ሚኒስትሩ መናገራቸውን ዘገባው አካቷል። ይሁንና ከአቀማመጡና ከውሃ ፍሰቱ አኳያ የእነዚህን አምስቱ የሃይል ማመንጫ ተርባይኖች ሃይል የማመንጨት አቅም አሁን ላይ ይህን ያህል ነው ብሎ መናገር እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በ13ቱ ተርባይኖች 5 ሺህ 150 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይልን ወደ ብሄራዊ የሃይል ቋት እንደሚቀላቀልም ነው ሚኒስተሩ የገለጹት፡፡ በዚህም÷ እያንዳንዳቸው ተርባይኖች በአማካይ ከ375 በላይ ሜጋ ዋት ሃይልን ያመነጫሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

5ቱ ተርባይኖች ወደ ስራ ሲገቡ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያላትን 4 ሺህ 818 ሜጋ ዋት የሃይል አቅርቦት መጠን ከፍ ያደርገዋልም ብለዋል፡፡

ኢትዮጰያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረች ድፍን 12 አመታትን አስቆጥራለች፡፡ ይህ ታላቅ ተስፋ የተጣለበት የህዳሴ ግድብ ጳጉሜን 5፣ 2015 ዓ.ም. አራተኛው እና የመጨረሻው የውሃ ሙሌት የመጠናቀቁ ብስራት ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በስተላለፉት መልዕክት “ብዙ ፈተና ነበረው፤ ወደኋላ እንድንመለስ ብዙ ተጎትተን ነበር። በውስጥ ፈተና በውጭ ጫና ነበረብን። ከፈጣሪ ጋር የመጣውን ሁሉ ተቋቁመን ለዚህ ደርሰናል።” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ እና የመጨረሻው የዉሃ ሙሌት መጠናቀቁን ማብሰራቸውን ተከትሎ ግብፅ ድርጊቱን “ህገ-ወጥ” ስትል መቃወሟን መዘገባችን ይታወሳል። ኢትዮጵያ የወሰደችው የአንድ ወገን ተግባር የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ግብዕ እና ሱዳን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያደርስ መሆኑን በመግለፅ የውሃ ሙሌቱ ህገ-ወጥ ነው ሲሉ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተቃውሞ ድምፅ ማሰማታቸው በዘገባው ተካቷል፡፡ አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button