ዕለታዊፍሬዜናፖለቲካ

ዕለታዊ ዜና፡ የኢዜማ ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ ወደ አዋሽ አርባ መዘዋወራቸውን እንደሰማ ፓርቲው አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29/ 2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ ወደ አዋሽ አርባ ወታደራዊ ማቆያ ማዕከል መዘዋወራቸውን ከቤተሰባቸው መስማቱን ፓርቲው አስታወቀ፡፡

ኢዜማ ትላንት መስከረም 28፣ 2016 ባወጣው መግለጫ ከተጠርጣሪው ቤተሰቦች ጋር በመወያየት አካልን ነጻ የማውጣት መደበኛ ክስ በቤተሰቡ አማካይነት መመስረቱን አስታውሶ የፌደራል ፖሊስ ትላንት መስከረም 28/2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ላይ ተጠርጣሪውን እንዲያቀርብ ቢታዘዝም ሳያቀርብ ቀርቷል ሲል ገልጧል፡፡

ፍርድ ቤቱ የፌደራል ፖሊስ ተጠርጣሪውን ለችሎት በማቅረብ፣ ለምን እንደያዛቸው እና ለምን እንደማይለቃቸው እንዲያስረዳ ትዕዛዝ ሲሰጥ የትላንትናው ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑን ያስታወቀው ድርጅቱ ፌደራል ፖሊስ በበኩሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስለሆነ እንዳላቀረባቸው እና ሊፈታቸውም እንደማይችል ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ መልስ ሰጥቷል ብሏል።

ፍርድ ቤቱም ትላንት በዋለው ችሎት በድጋሚ ለመስከረም 30/2016 ዓ.ም. ከዚህ ቀደም ትዕዛዝ እንዲያደርስ የታዘዘው ፖሊስ ታስሮ እንዲቀርብ እና ተጠርጣሪውም ችሎት ፊት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል ነው የተባለው።

ፖሊስ የመጀመሪያውን ትዕዛዝ ካለማክበር ጀምሮ ዛሬም በድጋሚ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት አለመፈጸሙ በፍትህ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ የሚፈጥር መሆኑን የገለፀው ኢዜማ ተቋሙ ህግ እና ሥርዓትን ብቻ ተከትሎ እንዲሰራ ጠይቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ሊቀመንበር ዶ/ር ጫኔ ከበደ በፀጥታ አካላት በቁጥጥር ስር የዋሉት መስከረም 13/2016 ዓ.ም ሲሆን ፓርቲው መስከረም 21 ቀን ባወጣው መግለጫ ዶ/ር ጫኔ ከበደ በጸጥታ አካላት በቁጥጥር ሥር የዋሉት በፓርቲው ባላቸው ኃላፊነት ሳይሆን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሠረት በኮማንድ ፖስቱ በመጠርጠራቸው ነው ሲል መግለፁ ይታወሳል፡፡አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button