ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ማይክ ሀመር በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ጉዳይ ለመምከር ወደ ካምፓላ እና አዲስ አበባ እንደሚያቀኑ ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 9/2016 .ም፡ የአሜሪካን መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር በኡጋንዳ ካምፓላ እና በአዲስ አበባ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አስታወቀ።

ማይክ ሀመር ወደ ሁለቱ ሀገራት ከጥር 8 ቀን 2016 እስከ ጥር 15 ቀን 2016 በሚያደርጉት ጉብኝት በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን ጉዳይ እንደሚመክሩ መስሪያ ቤቱ ጠቁሟል።

በኡጋንዳ ካምፓላ በሚካሄደው የኢጋድ አባል ሀገራት 42ኛው አስቸኳይ የመሪዎች ስብሰባ ላይ በመገኘት ከአባል ሀገራቱ መሪዎች ጋር በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል ስለተፈጠረው ውጥረት እንዲሁም ስለ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ዙሪያ እንደሚመክሩም አስታውቋል።

አሜሪካ ኢጋድ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት እንደምታደንቅ ያመላከተው የመስሪያቤቱ መግለጫ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1960 የተካለለውን የሶማሊያ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት አሜሪካ እውቅና እንደምትሰጥ በድጋሚ ማሳሰብ ትወዳለች ብሏል።

ሱዳን ጋር በተያያዘ ሀመር በቀጠናው ሀገራት እና አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚያደርገውን ሰላማዊ ጥረት በመደገፍ እና የሰብአዊ እርዳታ ያለምንም ገደብ በሚዳረስበት ሁኔታ ላይ ግፊት እንደሚያደርጉ መግለጫው አስታውቋል።

በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ በፕሪቶርያው ስምምነት ዙሪያ ከሀገሪቱ ባለስልጣናት ጋር ይመክራሉ ያለው የመስሪያ ቤቱ መግለጫ በተለይም የታዋጊዎችን ትጥቅ ስለማስፈታት፣ መበተን እና መልሶ ማቋቋም (DDR) በተመለከተ እንዲሁም ተጎጂዎችን መሠረት ስላደረገው የሽግግር ፍትህ ሂደት ይመክራሉ ብሏል።

ማይክ ሀመር በአማራ እና በኦሮምያ ክልሎች የሚካሄዱ ግጭቶች እና ጦርነቶችን ምክንያት የሚስተዋለውን የጸጥታ ችግር በማስቆም ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ለማስቻል ጥረት ያደርጋሉ ተብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በሌላ ዜና በኡጋንዳ በሚካሄደው የኢጋድ አባል ሀገራት 42ኛው አስቸኳይ የመሪዎች ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሸክ መሀመድ ካምፓላ መግባታቸው ተገልጿል።

ኢትዮጵያ፤ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግታት ድርጅት (ኢጋድ) በዛሬው ዕለት ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም በሚያካሄደው ጉባዔ ላይ “በተደራራቢ መርሀ ግብር” ምክንያት መገኘት የማትችል መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ማሳወቋን ዘገባችን ይታወሳል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button