ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ መግለጫን በጥብቅ እንደምትቃወም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ

አዲስ አዲስ አበባ፣ ጥር 9/ 2016 ዓ/ም፦ የአረብ ሊግ በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መካከል የተደረሰውን የመግባቢያ ሰነድ በተመለከት በትላነተናው ዕለት ያወጣውን መግለጫ ኢትዮጵያ በጥብቅ እንደምትቃወም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አስታወቁ።

አምባሳደር ምስጋኑ የአረብ ሊግ በጉዳዩ ላይ ያወጣው መግለጫ፤ “በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እና ሉዓላዊነት ላይ ጣልቃ የመግባት ሙከራ ነው” ሲሉ ተቃውመዋል። 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምዳሳደር መለስ አለም(ዶ/ር) በበኩላቸው የአርብ ሊግ መግለጫ “ተቀባይነት የሌለው” እና ኢትዮጵያ “በጥብቅ የምትቃወመው” መሆኑን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። “አፍሪካዊያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የምፍታት አቅም አላቸው” ሲሉም አምባሳደሩ ተናግረዋል። 

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪም በሊጉ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር  ኢትዮጵያ “በአካባቢው አለመረጋጋት እየፈጠረች ነው” የገለጹትን በተመለከተ፤ አምባሳደሩ “ኃላፊነት የጎደለው” ሲሉ ተችተዋል።  ቃል አቀባዩ “አርብ ሊግ እና ግብጽ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ናቸው” ብለዋል።

በሶማሊያው ፕሬዘዳንት ጥያቄ ትላንት ጥር 8/ 2016 በካይሮ የመከረው የአረብ ሊግ፤ ኢትዮጵያና ዓለም አቀፍ እውቅና ያላገኘችው ሶማሌላንድ የተፈራረሙትን የወደብ ስምምነት ዓለም አቀፍ ሕግን በግልጽ የጣሰ ሲል አወግዟል። 

በቅርቡ ኢትዮጵያ እና ሶማሊ ላንድ ኢትዮጵያ 20 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የባህር በር ለ50 ዓመታት ከሶማሌላንድ በሊዝ እንድትከራይ የሚፈቀድ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል። በስምምነቱ መሰረት ኢትዮጵያ ለሶማሊ ላንድ አውቀና ትሰጣለች።

የአረብ ሊግ ዋና ጸሐፊ አህመድ አቦል ገሀይት ስምምነቱን “የሶማሊያን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚጋፋ” ሲሉ ተቃውመው የመግባቢያ ሰነዱ ይዘት የአረብ የአፍሪካና የዓለም አቀፍ መርሆችን ላይ በግልጽ የተሰነዘረ ጥቃት ነው ብለዋል። በስብሰባው ላይ የተገኙት የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሚ ሽኩሪም ኢትዮጵያ በአካባቢው ያለመረጋጋት ምንጭ እየሆነች ነው ሲሉ ወቅሰዋል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

አምባሳደር ምስጋኑ ይህንን ተከትሎ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ መግለጫን እንደምትቃወም ባሳወቁበት መልዕክት ኢትዮጵያ ከብዙ የአረብ ሀገራት ጋር ጥሩ የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዳላት ነገር ገን የአረብ ሊግ የጥቂቶችን ጥቅም ብቻ እያስከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button