ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ ተግባራዊ የተደረገው የመዋዕለ ህጻናት የትምህርት ካሪኩለም በወላጆች ዘንድ ቅሬታ ማስነሳቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥር 13/2016 ዓ.ም፡- ከዘንድሮ የትምህርት ዘመን ተግባራዊ የተደረገው የመዋዕለ ህጻናት የትምህርት ካሪኩለም በወላጆች ዘንድ ቅሬታ ማስነሳቱ ተገለጸ።

በአብዘሃኛው በአፍ መፍቻ ቋንቋ እና ጨዋታ ላይ ትኩረት አድርጓል የተባለው የመዋዕለ ህጻናት (ኬጂ) የትምህርት ካሪኩለም ህጻናት እስከ 20 ድረስ ያሉ ቁጥሮችን ብቻ እንዲያጠኑ የሚያደርግ መሆኑን በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ የተዘጋጀ የጀማሪ እንዲሁም አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ “የኬጂ” ተማሪዎች የመማሪያ መጽሐፍን ዋቢ በማድረግ ቢቢሲ አስነብቧል።

ዘንድሮ የኢትዮጵያ የ“ኬጂ” ተማሪዎች እና እንግሊዝኛ ተቆራርጠዋል ሲል የገለጸው ዘገባው ህጻናት እንደወትሮው ስማቸውን በእንግሊዘኛ መጻፍ እንደማይለማመዱ አስታውቋል።

የመዋዕለ ህጻናት ተማሪዎች “ኤ፣ ቢ፣ ሲ፣ ዲ…”ን በዜማ መቁጠር፣ “ኤ ፎር አፕል፣ ቢ ፎር ቦል…” እያሉ ቃላት መመሥረት ማቆማቸውንም የጠቆመው ዘገባው ከዚህ ዓመት ጀምሮ “ስፖክን ኢንግሊሽ” እና “ኢንግሊሽ ሊትሬቸር” ከ“ኬጂ” ተማሪዎች የትምህርት ዓይነቶች ውስጥ መሰረዛቸውንም አመላክቷል።

ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት የሚልኩት ወላጆች ግን የእንግሊዝኛ ትምህርትን ያስቀረው አዲስ ሥርዓተ ትምህርት እንዳልተዋጠላቸው ዘገባው አስታውቋል። ያነጋገራቸው ወላጆች የሰጡትንም አስተያየት አካቷል።

በአራት ዓመታቸው “ነርሰሪ” የሚገቡት ህጻናት፣ በስድስት ዓመታቸው ከ“ዩ ኬጂ” ሲመረቁ የሚያውቁት ብቸኛ የፊደል ገበታ “ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ…” የሚል መሆኑን ገልጿል።

እንግሊዝኛ በማስተማር ተመራጭ የሆኑት የግል መዋለ ህጻናት ከዚህ ዓመት ጀምሮ ሁሉንም ትምህርት የሚሰጡት በአካባቢው የአፍ መፍቻ ቋንቋ ብቻ መሆኑን ያስታወቀው ዘገባው በአዲሱ የትምህርት ሚኒስቴር አሠራር መሠረት ተማሪዎች እንግሊዝኛ ቋንቋን እንደ አንድ ትምህርት መማር የሚጀምሩት አንደኛ ክፍል ሲደርሱ እንደሆነ ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የኬጂ ተማሪዎች እንደ ቀድሞው ሂሳብ፣ አማርኛ ወይም አካባቢ ሳይንስ የሚባሉ የትምህርት ዓይነቶች አይኖሯቸውም ያለው ዘገባው በትምህርት አይነቶች ፋንታ ህጻናቱ የሚማሩት “ጭብጦችን” መሆኑን አመላክቷል።

በአዲሱ ካሪኩለም መሠረት ህጻናቱ እንደ ቀድሞው አብዛኛውን ጊዜያቸውን ክፍል ውስጥ ቁጭ ብለው ከሰሌዳ እና ከደብተር ጋር እንዲፋጠጡ አይፈለግም ሲል የገለጸው የቢቢሲ ዘገባ ዘንድሮ የኬጂ ተማሪዎች የሚማሩባቸው ዋነኛ መንገዶች ጨዋታ፣ መዝሙር እና ተረት መሆናቸውን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ለካሪኩለሙ ትግበራ ያዘጋጀው የመምህራን መምሪያ “ህጻናት የሚማሩት በጨዋታ ነው” እንደሚል አካቷል።

በአዲሱ ሥርዓት ምክንያት ከአሁን በኋላ አብዛኛውን የትምህርት ቤት ጊዜያቸውን በጨዋታ የሚሳልፉት የኬጂ ተማሪዎች፤ የሚማሩት የትምህርት ይዘትም መቀነሱን እና “ከአቅማቸው በታች እንዲማሩ እያደረገ ነው” መባሉንም አስታውቋል።

“ቁጥርን በተመለከተ አማርኛውንም እንግሊዝኛውንም እስከ መቶ ድረስ እንዲያውቁ ይደረግ እንደነበር የጠቆመው የቢቢሲ ዘገባ በዚህ ዓመት ግን ይህ ቀርቷል፣ በአዲሱ ካሪኩለም መሠረት ህጻናቱ በሦስት ዓመት ቆይታቸው ቁጥር የሚማሩት እስከ 20 ድረስ እንደሆነ በመምህራን መምሪያ መጽሀፉ ላይ መስፈሩን አመላክቷል።

በተያያዘ ዜና የትምህርት ሚኒስቴር ለሁሉም ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ጥር 9 ቀን 2016 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተናን አስመልክቶ በጻፈው ደብዳቤ በተፈጥሮ ሳይንስ እና በማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች የሚፈተኑት ስድስት የትምህርት አይነቶች ብቻ መሆኑን አስታውቋል።

ሁሉም የተፈጥሮ ሳይንስ እና የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች እንግሊዝኛ፣ ሒሳብ፣ እና ስኮላስቲክ አፕቲቲዩድ ቴስት የሚፈተኑ ሲሆን የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ተጨማሪ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪ፣ ባዮሎጂ ትምህርቶችን እንደሚፈተኑ አመላክቷል። የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ በተጨማሪነት የሚፈተኑት የትምህርት አይነቶች ታሪክ፣ ጂኦግራፊ እና ኢኮኖሚክስ መሆናቸውን አስታውቋል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button