ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ወደ ሶማሊ ላንድ መዲና ሃርጌሳ ሲበር የነበረ የኢትዮጵያ አውሮፕላን በሶማሊያ መንግሥት እንዲመለስ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ጥር 8/ 2016 ዓ/ም፡_ በቅርቡ ከኢትዮጵያ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ወደተፈራረመችው ሶማሊላንድ መዲና ሃርጌሳ ሲበር የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን የሶማሊያ አየር ክልል ውስጥ ከመግባቱ በፊት እንዲመለስ መደረጉን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ሃርጌሳ ሲጓዝ የነበረው አውሮፕላን ከሶማሊያ በኩል ፍቃድ የለውም በመባሉ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ ለማረፍ ተገዷል።

የበረራ መከታተየ በሆነው ፍላይትራዳር24 በተባለው ድረ ገጽ ላይ መመልከት እንደሚቻለው ዛሬ ጥር 8/2016 ዓ.ም. ሁለት በረራዎች ወደ ሶማሊያ ተደርገዋል። መደበኛው የበረራ ቁጥር ኢቲ372 ረፋድ 5 ሰዓት ላይ ሃርጌሳ ማረፉን ፍላይትራዳር ያሳያል።

ይሁን እንጂ የበረራ ቁጥር ኢቲ8372 የሆነው ዲ ሃቪላንድ-400 አውሮፕላን ጠዋት 2፡30 ከአዲስ አበባ ተስቶ ወደ ሃርጌሳ አቅጣጫ እየበረረ ሳለ የጂግጂጋ ሰማይ ላይ በመዞር ረፋድ 4፡30 አካባቢ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተመልሶ ማረፉን የቢቢሲ ዘገባ አመላክቷል።

የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን በወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ቁጥር ኢቲ8372 ፍቃድ ስላልነበረው ሃርጌሳ ላይ እንዳያርፍ መከልከሉን አስታውቋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው መስፍን ጣሰው የትኛው የአየር መንገዱ አውሮፕላን እንዲመለስ እንደተደረገ እና እንዲመለስ በተደረገው አውሮፕላን ተሳፍረው ስለነበሩት መንገደኞች ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ይሁን እንጂ የሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዳውድ አዌይሳ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን የያዘ አውሮፕላን ፍቃድ ስላልነበረው ወደ ሃርጌሳ እንዳይገባ ተከልክሏል ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ነገር ግን ወደ ተነሳበት መድረሻ እንዳይበር ተከልክሎ ጉዞው የተስተጓጎለውን አውሮፕላን በተመለከተ ንግግር ከተደረገ በኋላ በረራው ዳግም እንዲቀጥል መደረጉን ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ መስፍን ጣሰው ተናግረዋል።አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button