ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ ስድስት ሰዎችን የቀጠፈው ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ በጋምቤላ ክልል የምትገኘው ጎደሬ ወረዳ ወደ ሰላሟ መመለሷን ነዋሪዎች አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4/2015 .ም፡ በጋምቤላ ክልል ማጃንጋ ዞን ስር በምትገኘው የጎደሬ ወረዳ ሰኞ ዕለት ነሃሴ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ምሽት ላይ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች በሰነዘሩት ጥቃት ስድስት የወረዳዋ ነዋሪዎች ህይወት ተቀጥፏል። ስማቸው ለደህንነታቸው ሲሉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የወረዳዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቁት በአሁኑ ወቅት በወረዳዋ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ገልጸዋል።

በጥቃቱ ሰለባ ከሆኑት መካከል በወረዳዋ በሚገኙ የገጠር ቀበሌዎች ነዋሪ የሆኑ አራቱ ገበሬዎች በቤታቸው ባረፉበት ሰኞ ምሽት ታጣቂዎቹ በሰነዘሩት ጥቃት መገደላቸውን የወረዳዋ ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል። በነገታው የጥቃቱን ሁኔታ ለመመርመር የሄዱ ሁለት ነዋሪዎች በታጣቂዎቹ በተሰነዘረ ጥቃት መገደላቸውንም ጠቁመዋል።

ነዋሪዎቹ በተጨማሪም ተመሳሳይ ጥቃት በ1999 ዓ.ም ጳጉሜን ወር ላይ ተፈጽሞ እንደነበር ለአዲስ ስታንዳረድ ገልጸዋል።  ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ሌላ የወረዳው ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንገለጹት ጥቃቱን የፈጸሙት የማጃንጋ ማህበረሰብ አባላት ሲሆኑ ታጣቂዎቹ ግድያውን ለመፈጸም ያነሳሳቸውም የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ገበሬዎች መሬታችንን ያላግባብ ቀምተው እየተስፋፉ ነው በሚል መሆኑን አስታውቀዋል።

በትላንትናው እለት አርብ ጳጉሜን 3 ቀን 2015 ዓ.ም በወረዳዋ በምትገኘው ሜጤ ከተማ የዞኑ የጸጥታ ሃላፊዎች ከሰባት የአከባቢው ቀበሌ ነዋሪዎች ጋር በተደረገ ውይይት ጉዳዩን ለመመርመር እና ጥቃቱን የፈጸሙትን ለፍርድ ለማቅረብ መግባባት ላይ መደረሱን ጎደሬ ወረዳ መንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክ ገጹ አስታውቋል።  በውይይቱም በወረዳው ዘላቂ ሰላም ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታና የህዝቡን የእርስ በርስ ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተጠቁሟል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button