ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና: የትራፊክ ፖሊስ አባል በጥይት መመታቱን ተከትሎ በጋምቤላ ከተማ ውጥረት መንገሱ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 10/2016 ዓ.ም፡- በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በሆነችው ጋምቤላ ከተማ ትላንት ሰኞ መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም የትራፊክ ፖሊስ አባል በጥይት መመታቱን ተከትሎ ውጥረት መንገሱ ተገለጸ፤ የትራፊክ ፖሊስ አባሉ በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

በፖሊስ አባሉ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በከተማዋ የትራንስፖርት አቅርቦት መቋረጡ፣ ባንኮች እና ዋና ዋና መሰረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መዘጋታቸው ተገልጿል።

ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ የከተማዋ ነዋሪ ለአዲስ ስታንዳርድ እንዳስታወቀው ጥቃቱ የተፈጸው በከተማዋ በሚገኝ ግራንድ ሆቴል ፊት ለፊት በስራ ላይ የነበረ ቹል ጋትኮት የተባለ የትራፊክ ፖሊስ አባል ላይ ሲሆን አራት ሰአት ጠዋት ላይ ነው።

ጉዳት የደረሰበት የትራፊክ አባሉን ሆስፒታል ድረስ በመሄድ እንደጎበኙት የገለጹልን የአይን ምስክር ጥቃቱ የደረሰበት አንገቱ ላይ መሆኑን እና ቀዶ ጥገናት ሊደረግለት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ ይገኛል ብለዋል።

በከተማዋ ነዋሪ የሆነ ሌላኛው አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገረው በበኩሉ በከተማዋ ከፍተኛ ውጥረት መንገሱን አስታውቆ የፖሊስ አባሉ ተገድሏል የሚል ወሬ በከተማዋ መሰራጨቱን እና ጥቃቱን ያደረሱት ደግሞ የኑዌር ሚሊሻዎች ናቸው መባሉን ገልጿል።

ሁኔታውን ተከትሎ መሰረታዊ አልግሎቶች፣ ባንኮች፣ ትራንስፖርት እና ትምህርት መቋረጡን ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button