ዜናፖለቲካ

ዜና፡ 35 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባዲሱ አመት ግጭቶች በዘላቂነት እንዲፈቱ የሰላም ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጳጉም 1/ 2015 ዓ.ም፡- 35 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለ2016 ዓ/ም አዲስ ዓመት የሰላም ጥሪ አቀረቡ አቀረቡ፡፡ ድርጅቶቹ ዛሬ በጋራ ባወጡት መግለጫ መጪው አዲስ ዓመት መንግሥት ሁሉን ዐቀፍ የሰላም መድረክ በመፍጠርና ግጭቶችን በመከላከል፣ የሰላም እጦቱ በዘላቂነት የሚፈታበት የአጭር፣ የመካከለኛ፣ እና የረዥም ጊዜ መፍትሔዎች የሚቀየሱበት እንዲሆን የሰላም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል እና የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD) ያካተተው የድርጅቶቹ ጋራ መግለጫ ያሳለፍነው ዓመት የትግራይ ክልል ጦርነት በስምምነት መጠናቀቁን ጠቅሶ በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር የቀጠለው ውጊያ፣ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው እና ተባብሶ የቀጠለው ግጭት፣የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ ያለው አለመረጋጋት፣ በጋምቤላ ክልል ተደጋግሞ የሚስተዋለው የእርስ በርስ ግጭትና አለመረጋጋት መስተዋላቸውን አመላክቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የጅምላና የዘፈቀደ እስሮች፣ የጋዜጠኞች እና የመብቶች ተሟጋቾች መዋከብና እስራት፣ የአስገድዶ መሰወር ድርጊቶች፣ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ግድያ፣ ያለመከሰስ መብት ያላቸውነ የሕዝብ ተወካዮች ማሰር፣ በጥቅሉ የፖለቲካ ምኅዳሩን የሚያጠቡ ሁኔታዎች ያገባደድነው ዓመት ኹነቶች ጥቅል ገጽታዎች ናቸው ሲል የገለፁት ድርጅቶቹ በአዲሱ አመት እነዚህ ሁነቶች እንዳይፈጠሩ ጥሪዎችን አቅርበዋል። 

በዚህም መሰረት፣ አገር ዐቀፍ የሰላም መድረክ እንዲመቻች፣ገለልተኛ ምርመራና ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ ፆታዊ ጥቃቶች ተገቢው ትኩረት እንዲሰጠቸው፣ የተጋላጭ እና ግፉአን ጥበቃ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ እንዲረጋገጥ፣ የቅድመ ግጭት መጠቆሚያ እና መከላከያ ስርዓት እንዲኖር፣ የሰብዓዊ  ድጋፍ አቅርቦት ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል፣ የጥላቻ ንግግር እና የተዛቡ መረጃዎች ስርጭት እንዲቆም፣የሲቪክ ምኅዳሩ ጥበቃ እንዲደረግለት እና ባለድርሻ አካላት ለሰላም ግንባታ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ድርጅቶቹ በጦርነትና በተለያዩ ክልሎች በተከስቱ ግጭቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉ፣ ቤትና ንብረታቸው የወደመባቸው፣ በተፈናቃዮች የመጠለያ ካምፖች የሚገኙ እና ለርሃብና እርዛት የተጋለጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች አፋጣኝ፣ የማይስተጓጎል እና በቂ የሆነ የምግብ፣ የጤና አገልግሎት እና ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶች፣ በዘለቄታውም የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ በማናቸውም ሁኔታ ሳይገደቡ እና ሳይቆራረጡ በሚመለከታቸው አካላት ሊቀርቡላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል። 

በመጨረሻም አዲሱ የ2016 ዓመት  ግጭቶች የተወገዱበት፣ ሰብዓዊ መብቶች በአግባቡ የሚከበሩበት፣ ለጉዳት ተጋላጭ የሆኑ ዜጎች ሙሉ ጥበቃ የሚያገኙበት፣ የጥላቻ ንግግሮች የሚቆሙበት፣ የሕግ የበላይነት የሚረጋገጥበት፣ ለሰላም ግንባታ እና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መስፈን የዜጎች ንቁ ተሳትፎ የሚታይበት  እንዲሆን 35ቱ ድርጅቶች መልካም ምኞታቸውን አቅርበዋል።አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button