ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በነገው ዕለት በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሎ የነበረው ሰልፍ “በመንግስት ጫና ላልታወቀ ግዜ ተራዝሟል” ሲል አስተባባሪ ኮሚቴው ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29/2016 ዓ.ም፡- በነገው እለት እሁድ ኅዳር 30 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ለማካሄድ ተጠርቶ የነበረው ሰልፍ በመንግስት ጫና ምክንያት ላልታወቀ ግዜ ተራዝሟል ሲሉ የሰልፉ አስተባባሪዎች ገለጹ።

ሰልፉ ለሌላ ጊዜ የተላለፈው መንግስት የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላትን በማሰሩ እና አሉታዊ የተባሉ እርምጃዎች በመውሰዱ መሆኑን ኮሚቴው በአዲስ አበባ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። አራት የሰልፉ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት መታሰራቸውንም ገልጿል።

ሰልፉ የተጠራው “ጦርነት ይቁም! ሰላም ይስፈን!” በሚል መሪ ቃል የፖለቲካ ልዩነቶች በሰላም እንዲፈቱ በማለም እንደነበር የሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴው አስታውቋል። ኮሚቴው ይህንኑን ሰልፍ ለማካሄድ የሚመለከተውን የመንግስት አካል ባሳውቅም መንግስት ሰልፉን የማክሸፍ ስራ ሰርቷል ሲል ኮንኗል።

በተነበበውም መግለጫ “መንግስት ሰላማዊ ሰልፉን የተለያዩ ፀረ-ሰላም ሃይሎች ያዘጋጁት እንደሆነ በማስመሰል የሰልፉ ቀን የጸጥታ ሃይሎችን የማሰማራት ፍላጎት የሌለው መሆኑን በመግለጽ ሰላማዊ ሰልፉን አቅጣጫ በማሳት አደናቅፏል” ሲል የገለጸው ኮሚቴው በመሆኑም ኮሚቴው የሰልፉን ቀን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍ መገደዱን አስረድቷዋል፡፡

“የሰልፉ ዓላማ ግልጽ ነው፡፡ በአገራችን ጦርነት እንዲቆም በማድረግ የሚደርሰውን እልቂትና ውድመት ማስቀረት ነው፡፡ ሆኖም መንግስት የህዳር 30ውን አገር አዳኝ ሰልፍ ከመደገፍ ይልቅ ሰልፉን ከታለመለት ዓላማ ውጪ በመግፋቱ አስተባባሪ ኮሚቴው ለተወሰኑ ቀናት በመግፋት ሰልፉን በተሻለና በውጤታማ መንገድ ለማካሄድ መደምደሚያ ላይ ደርሷል” ሲል የመንግስትነ እንቅስቃሴ ተችቷል።

የኢትዮጵያ የደኅንነት የጋራ ግብረ- ኃይል ህዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን አዲስ አበባን የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ሴራ አክሽፊያለሁ ሲል መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።

የሽብር ተልእኮውን የተቀበሉት እና በቁጥጥር ስር የዋሉት ቡድኖች “በትጥቅ የታገዘ ግፍና ግድያ በመፈፀም በኦሮምያ እና የአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ከውጭ ሀይሎች ጋር በመተባበር” ነው ሲል መግለጹም በዘገባው ተካቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ግብረ – ኃይሉ በመግለጫው 97 ተጠርጣሪዎች በተከናወኑ ኦፕሬሽኖች በቁጥጥር ስር አውያለሁም ማለቱም ተመላክቷል።

ሰላማዊ ሰልፉን እሑድ ህዳር 30 ቀን 2016 ከአራት ሰዓት እስከ ስምንት ሰዓት እንዲካሄድ ብለን ነው የጠራነው፤ ዋና መልእክቱም ጦርነት ይቁም ሰላም ይስፈን ሚል ነው፤ ሀሳቡን ለሚደግፍ ማንኛውም ሰው ነው ጥሪው የቀረበው ሲሉ ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ ፖለቲከኛ የሺዋስ አሰፋ መናገራቸውን የጀርመን ድምጽ ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button