ዜናቢዝነስ

ዜና፡ ኢትዮጵያ የውጭ ዕዳዋን መክፈል የማትችልበት ደረጃ  ጫፍ ላይ ትገኛለች ተባለ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29/2016 ዓ.ም፡- ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ገበያ የሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ አከፋፈል ላይ ከአበዳሪዎቿ ጋር ያደረገችው ድርድር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የውጭ ዕዳዋን መክፈል የማትችልበት ደረጃ (ዲፎልት) ላይ ለመድረስ ጫፍ ላይ ትገኛለች ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።

ኢትዮጵያን የቦንድ ግዢዋን ከፈጸሙ ዋና ዋና ተቋማት ጋር ያደረገችው ድርድር ትላንት ህዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም ያለውጤት ተጠናቋል ያለው ሮይተርስ በአንድ ወቅት ፈጣን እድገት በማስመዝገብ ተስፋ ተጥሎባት የነበረች ሀገር አሁን ብድሯን መክፈል ተስኗታል ሲል ገልጿል።

ኢትዮጵያ ስትደራደራቸው ለነበሩ ዋና ዋና ቦንድ ገዢዎቿ ታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም መክፈል የሚጠበቅባትን 33 ሚሊየን ዶላር ወለድ መክፈል እንደማትችል መግለጿን ሮይተርስ የሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስቴርን ጠቅሶ በዘገባው አስታውቋል።

በታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም መክፈል የሚጠበቅባትን ወለድ አለመክፈሏ የውጭ ዕዳዋን መክፈል የማትችልበት ደረጃ (ዲፎልት) ላይ እንድትቀመጥ ያደርጋታል ሲል ዘገባው አትቷል።

እንዳለመታደል ሁኖ በቀሪዎቹ ቀናት ከአበዳሪዎቻችን ጋር ስምምነት ላይ መድረስ አንችልም ሲል የገንዘብ ሚኒስቴር ማስታወቁንም ዘገባው አካቷል።

የቦንድ ገዢዎች የመሰረቱት ኮሚቴ በበኩሉ ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን የወለድ ክፍያ መክፈል አልችልም ማለቷ አላስፈላጊ እና የማይጠበቅ ነው ሲል መተቸቱን አስታውቋል። ከመንግስ ባለስልጣናት ጋር ገንቢ እና አስቻይ ውይይቶችን ለማድረግ ዝግጁ ነን ሲል ኮሚቴው መግለጹንም አመላክቷል። ኢትዮጵያ ከቦንድ ገዢዎቿ ጋር በቀጣይ ሌላ የድርድር ማዕቀፍ አዘጋጅት እንደምትወያይ የገንዘብ ሚኒስቴር መግለጹን የዜና አውታሩ በዘገባው አስታውቋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button