ዜናፖለቲካ

ዜና፡ ኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ በአዲስ አበባ እየመከሩ ነው፣ አዳዲስ ስምምነቶችም ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ የካቲት 4/2016 ዓ.ም፡- ሶስተኛው የኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የጋራ የሚኒስትሮች ኮሚሽን ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተጠቆመ።

በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የጋራ ስብሰባው የሀገራቱን ሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና አዳዲስ ስምምነቶችን ለመፈራረም ያለመ መሆኑን የሩዋንዳው ኒው ታይምስ ጋዜጣ በድረገጹ አስነብቧል።

ለሶስት ቀናት የሚቆየው ስብሰባ በትላንትናው ዕለት በሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ሃላፊዎች ምክክር መጀመሩን ዘገባው ጠቁሟል።

በተመሳሳይ ትላንት የካቲት 3 ቀን 2016 ዓ.ም የተጀመረው የሁለቱ ሀገራት የከፍተኛ ሃላፊዎች ስብሰባ ለሶስተኛ ግዜ መደረጉን የጠቆመው የኢዜአ ዘገባ ስብሰባው በመካሄድ ላይ የሚገኘው በኢትዮጵያ በኩል በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ፍሰሀ ሻውል እና በሩዋንዳ በኩል ደግሞ የሀገሪቱ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሜጀር ጀነራል ጄን ቻርልስ ካራምባ በተገኙበት መሆኑን አስታውቋል።

የኢትዮ-ሩዋንዳ የሚኒስትሮች ስብሰባ ሀገራቱ በተለያዩ መስኮች የተፈራረሟቸውን ስምምነቶች ወደ ትግበራ ማስገባት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ የሚመክር መሆኑን አምባሳደር ፍሰሀ ሻውል መናገራቸውን ዘገባው አመላክቷል።

የሁለቱ ሀገራት የስራ ሀላፎዎች በአዲስ አበባ እያካሄዱት ባለው ስብሰባ አዳዲስ የትብብር ስምምነቶች ይፈራረማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የሩዋንዳው ኒው ታይምስ በድረገጹ አስነብቧል።

ሁለተኛው የሁለቱ ሀገራት የጋራ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሰባትአመታት በፊት በኪጋሊ በተፈራረመበት ወቅት የተደረሱ ስምምነቶች አፈጻጸም የሃላፊዎቹ የዘንደሮው ስብሰባ ዋነኛ አጀንዳ መሆኑን ድረገጹ አስታውቋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button