ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የሕዝብ በዓላትን አከባበር ለመወሰን የቀረበለትን ረቂቅ ጨምሮ ሶስት ውሳኔዎችን አሳለፈ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 10/2016 .ም፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬ ዕለት ታህሳስ 10 ቀን 2016 ዓ.ም ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች ማሳለፉን ከጽ/ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የመሬት ይዞታ የሚለቀቅበትን፣ ካሣ የሚከፈልበትን እና ተነሺዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን ሁኔታ ለመወሰን በቀረበው ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ መሆኑን አስታውቋል።  

መንግስት ለሕዝብ ጥቅም በሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ሲባል የመሬት ይዞታ እንዲለቁ ለሚደረጉ ባለይዞታዎች ተገቢና ተመጣጣኝ ምትክ ይዞታ፣ ካሣ መስጠትና ድጋፍ ማድረግ እንዲቻል ግምት ውስጥ መግባት የሚገባቸውን መሠረታዊ መርሆዎች ለመደንገግ፣ ካሣን የመተመን፣ የመክፈል እንዲሁም ተነሺዎችን መልሶ የማቋቋም ሥልጣንና ኃላፊነት የተጣለባቸውን አካላት እና ግዴታዎቻቸውን በግልጽ መድረግ በማስፈለጉ በስራ ላይ ያለውን አዋጅ ቁጥር 1161/2011 የሚያሻሽል ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ መቅረቡን ጠቁሟል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አመላክቷል።

በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየዉ የሜዳይ፣ ኒሻን እና ሽልማት ረቂቅ አዋጅ ላይ መሆኑን የጠቆመው ጽ/ቤቱ በልዩ ልዩ ዘርፎች የላቀ ተግባር ለፈጸሙ ዜጎች እና ግለሰቦች እዉቅና መስጠት፣ በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ለሀገር ለሚያበረክቱት የላቀ አስተዋጽኦ ኢትዮጵያ ባለዉለታ አድርጋ እንደምታከብራቸዉ እውቅና የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም የእነርሱን አርአያነት እንዲከተሉ የሚያበረታታ፣ የስራ ፈጠራ እንዲስፋፋ፣ ሁለንተናዊ እና ቀጣይነት ያለዉ ብልጽግና እንዲረጋገጥ ፋይዳው የላቀ በመሆኑ በኢፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት የተደነገገውን የሜዳይ፣ የኒሻን እና የሽልማት አሰጣጥ ስርዓት መተግበር የሚያስችል፣ ለአተገባበሩም ህጋዊ ሥርዓት የሚዘረጋ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መቅረቡን አስታውቋል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል እንዲጸድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አመላክቷል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የሕዝብ በዓላትን፣ የዕረፍት ቀናትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ መወያየቱን አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የሕዝብ በዓላት እና የእረፍት ቀናት ለዜጎች ሥነ-ምግባርና ስነ-ልቦና ግንባታ እንዲሁም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦዋችው ከፍተኛ በመሆኑ ሕጋዊ እውቅና መስጠት እና በብሔራዊ ደረጃ እንዲከበሩ ማድረግ የሚገባ በመሆኑ፤ ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ ሥርዓታቸውን ጠብቀው ሊከበሩ የሚገባ በመሆኑ፤ የዜጎችን የእርስ በእርስ መልካም ግንኙነትና መተሳሰብ የሚያጎለብቱ እንዲሆኑ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ መቅረቡን ጠቁሟል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል እንዲጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል ብሏል

በመጨረሻ ምክር ቤቱ የተወያየው በአምራች ኢንዱስትሪ ረቂቅ ፖሊሲ ላይ መሆኑን የጠቆመው ጽ/ቤቱ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት እና መዋቅራዊ ሽግግር መሳለጥ የላቀ ሚናውን እንዲወጣ፤ ለውጪ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ ከውጪ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እና ለዘላቂ የሥራ ዕድል ፈጠራ መደላድል የሚሆን የፖሊሲ ማእቀፍ ሚያስፈልግ በመሆኑ፤ የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ ለማሳደግና ለማበረታታት፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት በአካባቢና በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ክብካቤ መርሆዎቻችን ላይ የተመሰረተ እንዲሆን፣ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ያለውን ትስስርና ቅንጅት ለማሳደግ የሚያስችል ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጅቶ ምክር ቤቱ መቅረቡን አመላክቷል።

ምክር ቤቱም በረቂቅ ፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ መወሰኑን አስታውቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button