ዜናፖለቲካህግ እና ፍትህ

ዜና፡ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር “የሕገ – መንግሥት ጥሰት” አቤቱታ ቀረበበት

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/ 2016 ዓ/ም፦ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያወጣው ደንብ ቁጥር 4/2016 የኢፌዴሪን ሕገ – መንግሥት አራት አንቀጾችን የሚቃረን ነው በሚል ለሰብዓዊ መብቶች – ኢትዮጵያ የተባለው ሀገር በቀል የሲቪክ ድርጅት አቤቱታ አቀረበ። 

መቀመጫውን አዲስ አበባ ያደረገው የሲቪክ ድርጅቱ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ያወጣው ደንብ የሕገ- መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት ጉዳዩ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲላክ ለሕገ – መንግሥት አጣሪ ጉባኤ የዳኝነት አቤቱታ አቅርቧል። 

ድርጅቱ የአቤቱታው መነሻ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ያወጣው ደንብ በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት  “ኢ- ሕገ መንግሥታዊ ተብሎ የፈረሰው [የክልሉ] ምክር ቤት ያወጣቸው ሕጎች ተፈፃሚነታቸው እንዲቀጥል ያደረገ በመሆኑ” ነው ማለቱን ዶይቸ ቨለ ዘግቧል።  

አቤቱታው “በኢትዮጵያ እና በክልሉ ሕጎች መሠረት የተቀጠሩ፣ የሰለጠኑ፣ እና ለዓመታት ያገለገሉ የፖሊስ አባላት በትጥቅ ትግል አልተሳተፉም በሚል ከሥራ ማባረሩን ወይም ወደ ሥራ እንዳይመለሱ” እና ጡረታ መከልከላቸውን ይጠቅሳል።  

“ሕጉ የወጣው በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ሕገ – መንግሥታዊ አይደለም በሚል በፈረሰው የክልሉ ምክር ቤት በመሆኑ ተፈፃሚ ሊሆን አይችልም” ሲል የሲቪክ ድርጅቱ ጉዳዩን ለሕገ – መንግሥት አጣሪ ጉባኤ አቅርቦታል ተብሏል።

ቅድሚያ ለስብዓዊ መብቶች – ኢትዮጵያ የተባለው የሲቪክ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መብርሂ ብርሃነ የትግራይ ክልል ምክር ቤት በወጣ ዐዋጅ መሰረት የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ ከ 1 ሺህ በላይ የትግራይ ክልል ፖሊስ አባላት የነበሩ ሰዎች ከሥራ ተባረው በችግር ላይ መሆናቸው የአቤቱታው መነሻ ነው ብለዋል።

በክልሉ ወጥተው በነበሩ የአስቸካይ ጊዜ ሕጎች ፍርደኛ ሆነው በእሥር ላይ የሚገኙ ሰዎች ወደ ፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ በመሄድ የይግባኝ መብታቸውን እንዳይጠቀሙ የሚከለክል መሆኑ ሌላኛው ተጨማሪ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ይህንን ደንብ ሊያወጣ የቻለበት ምክንያት “ከመንግሥት ሠራተኞች እና ከግል ሠራትኛች ጋር ተያይዞ የደሞዝ ጥያቄ በየጊዜው እየተጠየቁ ሲመጡ ይህንን በሕግ አውጥተን ለምን አንገድበውም የሚል አቋም የወሰዱ ይመስልኛል”  ሲሉ አቶ መብርሂ ግምታቸውን ገልፀዋል ሲል የዜና አውታሩ በዘገባው አካቷል።

ሕዳር 28 ቀን 2016  ዓ. ም በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የተፈረመው እና “ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕጎች ወደ መደበኛ ሕግ ለመምለስ የወጣ የመሸጋገሪያ ደንብ” በሚል የወጣው ሕግ “ወደ መደበኛ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መመለስ እና የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መጠናከርን ሊያግዝ የሚችል እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት” ይህ ደንብ መውጣቱን ይገልፃል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button