ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና: “አቶ ጌታቸው ረዳን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንትነት አንስቻለሁ” ሲል በዶ/ር ደብረጺዮን የሚመራው ህወሓት አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27/2017 ዓ.ም፡- በዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን ዛሬ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሁነው በማገልገል ላይ ያሉትን አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ አምስት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላትን ከስልጣን አንስቻለሁ ሲል አስታወቀ።

በአቶ ጌታቸው ረዳ ምትክ “የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት የሚሆኑትን አመራር ከፌደራል መንግስቱ ጋር በመነጋገር አሳውቃለሁ” ሲል ገልጿል።

ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳን ጨምሮ በጊዜያዊ አስተዳደሩ በካቢኔ አባልነት እና የተለያዩ ቢሮ ሃላፊ ሁነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ባለስልጣናት ከዛሬ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ “ምንም አይነት አመራር መስጠት፣ ውሳኔ ማሳለፍ አይችሉም” ሲል ገልጿል።

ይህንንም “መንግስታዊም ይሁን መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር አካላት፣ የትግራይ የፀጥታ አካላት፣ የፌደራል መንግስቱ እና ክልሎች፣ አለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ሌሎች የሚመለከቱ አካላት እንዲያውቁልን እናሳስባለን” ብሏል።

በዶ/ር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን ከስልጣናቸው አንስቻቸዋለሁ ባላቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ አባላት ምትክ አዲስ ተሿሚወችንም አስታውቋል።

በተጨማሪ በክልሉ ለሚገኙ ስድስት ዞኖች የሾማቸውን አመራሮችም በዝርዝር አስቀምጧል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሲቋቋም 51 በመቶ የሚሆኑት የህወሓትን የካቢኔ ድርሻ የያዙ መሆናቸውን ያመላከተው የእነ ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) መግለጫ የካቢኔ አባላት በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ በየነ ምክሩ፣ ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ህይወት፣ ዶ/ር ሓጎስ ጎደፋይ እና ወ/ሮ ኣልማዝ ገ/ፃድቕ ከሃላፊነት ተነስተዋል ብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በምትካቸውም የቀድሞ የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር አብርሃ ተከስተን ጨምሮ ሰባት አመራሮችን መሾሙን አስታውቋል።

የጊዜያዊ አስተዳደሩ ተልዕኮ “ሰላምና ፀጥታን ማስጠበቅ፣ ማገገምና መልሶ ማቋቋም ስራ መስራት፣ የፕሪቶሪያ ስምምነትን በአግባቡ መተግበር፣ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና በአጭር ጊዜ ገደብ ውስጥ በክልሉ በዲሞክራሲያ መንገድ በህዝብ የተመረጠ መንግስት እንዲመሰረት ሁኔታዎችን ማመቻቸት እና ምህዳር መፍጠር ነው” ሲል መግለጫው አትቷል።

ግልጽ ተልዕኮ እና አደረጃጀት ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ “በጥገኛ ቡድን ተጠልፎ፣ ከተቋቋመለት ዓላማ ወጥቶ፣ ያለ ዕቅድና አቅጣጫ እየተመራ እዚህ ደርሷል” ያለው መግለጫው በተጨማሪም አስተዳደሩ “የሥልጣን ጥመኞች ወኪል በመሆን እያገለገለ ነው” ሲል ተችቷል።

“በጊዜያዊ አስተዳደሩ ስር ተደብቆ የሚገኘው ቡድን የትግራይ የጸጥታ ሀይሎችን በስሩ በማድረግ እራሱን ወደ ወታደራዊ አንባገነን ስርአት ለመቀየር ጥሯል” ሲል ኮንኗል።

“ቡድኑ ተጨማሪ የስልጣን ጊዜ ባገኘ ቁጥር ሌሎች መዘዞችን እና ብሔራዊ ጥፋት የሚያመጣ ለመሆኑ ግልጽ ሁኗል” ሲል አትቷል።

በደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መስከረም 14 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ “በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ ያሉ መሰረታዊ ችግሮችን ለመፍታት ወደ ተግባር እገባለሁ” ሲል ማስታወቁን መዘገባችን ይታወሳል።

የትግራይ ክልል የጸጥታ አካላት በጊዜያዊ አስተዳደሩ እየተመሩ ይሰራሉ ሲል በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ተከትሎ በደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የሚመራው ህወሓት “የጊዜያዊ አስተዳደሩ “የትግራይ ሰራዊትን በስሩ በማድረግ ማዘዝ አይችልም” ሲል መግለጹም ይታወሳል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button