ዜናፖለቲካ

ዜና: መንግስት በተያዘው አመት "የሃይል አማራጭን በመጠቀም ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ለሟሟላት የሚደረጉ ጥረቶችን አይታገስም” - ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27/2017 ዓ.ም፡- “የሃይል አማራጭን በመጠቀም ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ለሟሟላት የሚደረጉ ማናቸውንም እኩይ ተግባራት መንግስት በልበ ሰፊነት የሚያልፍበት ዕድል እጅግ የጠበበ ነው” ሲሉ አዲስ የተመረጡት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አስታወቁ።

6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት በዛሬው ዕለት መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም ተካሂዷል።

የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ የመጨረሻ የመክፈቻ ንግግር የሚጠበቅበት የሁለቱ ምክር ቤቶች ሥብሰባ ቢጠናቀቅም የቀድሞዋ ፕሬዝዳንት ምንም አይነት ንግግር ሳያደርጉ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ሆነው ሲያገለግሉ ለነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ሃላፊነታቸውን አስረክበዋል።

በዚህም አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው በዛሬው ዕለት ተሹመዋል፡፡

በዚሁ ወቅት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ታዬ አጽቀሥላሴ የመንግስትን ቀጣይ አመታዊ አቅጣጫ በሚያመላክተው ንግግራቸው “መንግሥት ዛሬም ድረስ የሰላም በሮቹ ወለል ብለው እንደተከፈቱ ናቸው” ሲሉ ገልጸዋል።

“በተናጠል ይሁን በጋራ ሰላማዊ ውይይት ለማድረግ መንግሥት ሁልጊዜ ዝግጁ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ነገር ግን “ከዚህ ውጪ የሃይል አማራጭን በመጠቀም ፖለቲካዊ ፍላጎቶችን ለሟሟላት የሚደረጉ እኩይ ተግባራትን መንግሥት በልበ ሰፊነት የሚያልፍበት ዕድል እጅግ የጠበበ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም “ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ምድር ሃይልን በብቸኝነት መጠቀም መብት የመንግስት ተቋማት ብቻ  መሆኑን ማረጋገጥ ይገባል” ብለዋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪ “ሁሉን አካታች” ሃገራዊ ምክክር በመድረግ ላይ እንደሚገኝ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አንስተዋል።

“ከንዑስ ነጠላ ትርክት ወደ ታላቅ ብሔራዊ ትርክት መሻገር አለብን” ያሉት ፕሬዝዳንቱ “አሰባሳቢ እና ሃገራዊ ገዢ ትርክትን በሁሉም ኢትዮጵያውያን: ለሁሉም ኢትዮጵያውያን: ከሁሉም ኢትዮጵያውያን እንዲሆን ለማስቻል ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በመሰራት ላይ ይገኛል” ሲሉ ገልጸዋል።

የፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ የሥራ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ መንግሥት ከ”ለውጡ ማግስት” ጀምሮ አመርቂ የኢኮኖሚ ስራዎችን ሲሰራ ቆይቷል ሲሉ በንግግራቸው አመላክተዋል።

“ኢኮኖሚያችን በአዲስ እጥፋት ላይ ይገኛል:” ያሉት ፕሬዝዳንቱ አክለውም አሁን ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ “ከነጠላ ዘርፍ ወደ ብዘሐ-ዘርፍ እየተሸጋገረ ነው:” ሲሉ ተደምጠዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ አክለውም ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመጠገን የምታደርገው ጥረት አበረታች ነው ብለዋል።

በተጨማሪ ባለፉት ዓመታት በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በኢንቨስትመንት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን አመላክተዋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button