ዜና

ሰበር ዜና፡ ለረጅም አመታት በኃላፊነት ያገለገሉት ደመቀ መኮንን ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትር፣ ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር እና ከብልጽግና ፓርቲ ኃላፊነታቸው ተሸኙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17/ 2016 ዓ/ም ፦ ለረጅም አመታት በከፍተኛ የመንግስት በኃላፊነት ያገለገሉት አቶ ደመቀ መኮንን ከምክትል ጠቅላይ ሚንስትር እና ከውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኃላፊነታቸው መሸኘታቸውን ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊ ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

በተጨማሪም ከጥር 15፣ 2016 ዓ/ም ጀምሮ  የስራ አስፈጻሚ እና ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ እያካሄደ ያለው ገዢው ብልጽግና ፓርቲ አቶ ደመቀ መኮንን ከፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ኃላፊነታቸው ሸኝቷል።

በምትካቸውም የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትን አቶ ተመስገን ጥሩነህን ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ በአብላጫ ድምጽ መርጧል። 

አቶ ደመቀ መኮንን በፌዴራል ደረጃ የኃላፊነት ስራ የጀመሩት 2000 ዓ/ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስተዳደር ወቅት የትምህርት ሚኒስትር በመሆን ነበር።   የትምህርት ሚንስትር ሆነው ከመሾማቸው ቀደም ብሎ የአማራ ክልል የስነ ምግባር እና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው አገልግለዋል። በተጨማሪም የክልሉ የአስተዳደር እና የጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊም ሆነው ሰርተዋል።  ከ1997 እስከ 2000 ድረስ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ በመሆን አገልግለዋል። ከዚያ በኋላ በ2000 ዓ/ም የትምህርት ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አቶ ደመቀ በዚህ ኃላፊነት እስከ ኃምሌ 2005 ዓ/ም አገልግለዋል። በመቀጠል 2005 ዓ/ም ወደ ሚኒስትር ስልጣን ደረጃ አድገዋል። 

በቀደሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ አስተዳደር ወቅት መስከረም 2005 ዓ/ም  ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ከተሾሙበት ግዜ አንስቶ እስከ አሁን በዚህ ኃላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል። 

አቶ ደመቀ መኮንን የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እና ህልውናው ታህሳስ 2011 ዓ.ም እካከተመበት ድረስ የኢትዮጵያ ህዝቦች አበዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ምክትል ሊቀመንበር ሆነው በሃላፊነት ሰርተዋል።  አገሪቱን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ገዢው ፓርቲ ብልጽግና ከተቋቋመበት ግዜ ጀምሮ ሁለተኛው የፓርቲው ፕሬዝዳንት ሁነው አገልግለዋል።አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button