ቃለ መጠይቅ
በመታየት ላይ ያለ

ቃለ ምልልስ : “አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሀብታሞች ብቻ ተቋም አይሆንም”- ዶ/ር ማቲዎስ ኢንሰርሙ የአአዩ ም/ፕሬዝዳንት

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 20/2015 ዓ.ም፡- የሚኒስትሮች ምክር ቤት ካሳለፋቸው ታላላቅ ውሳኔዎች መካከል አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሀገሪቱ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ እንዲሆን ያሳለፈው ውሳኔ ይገኝበታል። ዩኒቨርስቲው ለዚህ የበቃው የትምህርት ሚኒስቴር በቀጣይ ሁለት አመታት የመጀመሪያው የሀገሪቱ የዩኒቨርስቲ ትውልድ ተደርገው ከሚቆጠሩት ውስጥ አስሩ የራስ ገዝነት ደረጃ እንዲያገኙ እንደሚደረጉ  ማሳወቁን ተከትሎ ነው።

የራስ ገዝ መሆኑንም ተከትሎ በቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን እንዴት እንደሚቀበል መግለጫ ሰጥቷል። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከመጪው 2016 ዓ.ም ጀምሮ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን የሚቀበለው በምደባ ሳይሆን በውድድር መሆኑን አስታውቋል። ዩኒቨርስቲው ከፍያ የሚፈጽመው የቅድመ ምርቃ ተማሪዎችን በልዩ ሁኔታ ለማስተማር እንዳቀደም ገልጿል።

አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተያያዘውን የለውጥ ሂደት አስመልክቶ የአዲስ ስታንዳርድ ጋዜጠኛ ዘላለም ተክሌ የዩኒቨርስቲው  ምክትል ፕሬዝዳንት ከሆኑት እና በአስተዳደራዊ እና አካዳሚ ዘርፎች ለአስራ ስምንት አመታት ያገለገሉትን እንዲሁም ለዩኒቨርድቲው ታላቅ አበርክቶ ከሰጡት አንዱ የሆኑትን ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ማቲዎስ ኢንሰርሙ የማነጋገር እድል አግኝቷል።

አስ: የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔን ተከትሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሀገሪቱ የመጀመሪያው ራስ ገዝ ዩኒቨርስቲ ሁኗል፤ የዚህ ለውጥ አንድምታው ምንድን ነው? ምን ለውጥ ያመጣል?

ዶ/ር ማቲዎስ: ራስ ገዝ መሆኑ ለዩኒቨርስቲው ጥልቅ ትርጉም አለው። በሌሎች መንግስት መር በሁኑ ተቋማት እንደ አየር መንገድ እና ኢትዮቴሌኮም የተካኑ የቦርድ አባላት እና ከፍተኛ አፈጻጸም ያላቸው ስራ አስፈጻሚዎች ካገኘ ስኬቱ ያሳድገዋል። ይህ ለአዲስ አበባ ዩኒቨረስቲ የተሰጠው ልዩ መብት ጠንካራ የቦረድ አባላትን አና ብቃት ያላቸውን ሰራ አሰፈጻሚዎችን ለመመልመል ያስችላል። ይህም በአለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ደረጀ ተወዳዳሪ እንድንሆን ያግዘናል። በተጨማሪም ራስ ገዝ መሆናችን እስትራቴጂያዊ እቅዶቻችንን እና መመሪያዎቻችንን እንድንቀይስ ስልጣን ይሰጠናል። ለምሳሌ ያክል የፋይናንስ ቢሯችን የቅጥር ሁኔታዎችን በተመለከተ የዩኒቨርስቲውን አላማ የተመረኮዘ መመሪያ ማዘጋጀት ያስችለዋል። ይህም የደመወዝ ስኬላችንን ለመወሰን ያስችለናል፤ ተወዳዳሪነታችንን ሊያስጠብቁ የሚችሉ ታላላቅ ፕሮፌሰሮችን ለመሳብ ይረዳናል።

ምንም እንኳን ሀገራዊ ግዴታዎቻችንን ለመወጣት በሚል እና በመንግስት ወደ ዩኒቨርስቲያችን የሚመደቡ ተማሪዎች ስለሚኖሩ ከመንግስት የምናገኘው ድጎማ የሚቀጥል ቢሆንም ራስ ገዝ መሆናችን የሚሰጠንን ድጎማ ምን ላይ ማዋል እነዳለብን የመወሰን ስልጣን ያላብሰናል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪም ዩኒቨርስቲው ቀጣይነት ያለው ገቢ የሚያስገኙ የራሱን የቢዝነስ መንገድ ተከትሎ በሞያ የንግድ ድርጅቶችን ማቋቋም ይችላል። በኢንጂነሪንግ በአማካሪነት የሚሰሩ ተቋማት እና የግል ሆስፒታል ተጠቃሽ ናቸው።  በእንደዚህ አይነት አካሄዶቸ በመከተል በቂ የሆነ ገቢ ለማመንጨት ስንንቀሳቀስ መረሳት የሌለበት ነገር ገቢው የዩኒቨርስቲውን ተልእኮውን ለመወጣት፣ እድገቱን ማስቀጠል እና የትምህርት ልህቀቱን ማስቀጠል ላይ እንዲውል እንደሚደረግ ነው።

አስ: በቅርቡ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከቀጣይ አመት ጀምሮ ዩኒቨርስቲው የሚቀበለው ተማሪ በመግቢያ ፈተና በመስጠት ነው። ለዚህ ውሳኔ ያደረሳችሁ ምክንያት ምን እንደሆነ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የመፈተን እድሉ እንዲዳረስ ለማስቻል ምን እየተሰራ እንዳለ ቢያብራሩልን?

ዶ/ር ማቲዎስ: የመግቢያ ፈተና ተኮር ቅበላ ሂደት ላይ እንድናተኩረ ያደረገን ዋናው መሰረቱ ራስ ገዝ እንድንሆን ያሰጠን አዋጅ ነው። ከዚህ በፊት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ምደባ የሚከናወነው በትምህርት ሚኒስቴር ነበር። ምንም እንኳ አንዳንድ በዩኒቨርስቲያችን የሚመደቡ ተማሪዎቸ በቂ ዘግጅት ያደረጉ አንደሚገኙ የሚጠበቅ ቢሆንም አንዳንዶቹ ደግሞ የእኛን የትምህርት ደረጃ የማይመጥኑ ደካማ የሆኑ ተማሪዎች ይመጣሉ።  

በፈተና የመቀበል አካሄድን የተከተልንበት ዋነኛ አላማ ብቃት ያላቸውን ታማሪዎች ለመለየት ነው። መታወቅ ያለበት ዋነኛ ነገር ይህ አካሄድ ከትምህርት ሚኒስቴር የቅርብ ፖሊሲ ጋር የሚዛመድ ነው። የመውጫ ፈተና ተጀምሯል፤ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የመንቀበላቸው ተማሪዎችን መመዘን አለብን።

አፈጻጸሙን በተመለከተ የተለያዩ መንገዶችን ለመጠቀም እያጠናን እንገኛለን። አንደኛው መንገድ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙትን ዩኒቨርስቲዎች እንደ መፈተኛ ማዕከል መጠቀም ነው። ይህም በሁሉም ክልሎች የሚገኙ ተማሪዎች እድሉን እንዲያገኙ ያስችላል።  በተጨማሪም በኦንላይን ፈተናውን ለመስጠት ሀሳብ አለን።

አስ: የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት በቅርቡ ያሳወቁት ጉዳይ ትኩረት አግኝቷል፤ ይህም ገንዘብ ከፍለው ለየት ባለ ሁኔታ መማር ይችላሉ የሚለው። ገንዘብ ያለው ገብቶ መማር ይችላል የሚል እሳቤ አሳድሯል እና ምላሻችሁ ምንድነ ነው

ዶ/ር ማቲዎስ: አዋጁ ይህ አይነቱን ውሳኔ ለማሳለፍ ሙሉ ስልጣን ሰጥቶናል። የሀብታም ብቻ ዩኒቨርስቲ አይደለም የሚሆነው፤ ሁልጊዜም ብዝሃነትን ማስቀደም ላይ ትኩረት እንሰጣለን ይህንንም እናስቀጥላለን።

በመጀመሪያ ደረጃ መታወቅ ያለበት ከየትኛውም ማህበረሰብ ክፍል ይምጣ ማንኛውም ተማሪ የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ወስዶ ያለፈ ሁሉ የዩኒቨርስቲያችንን የመግቢያ ፈተና የመውሰድ መብት አለው። ሀብት ባይኖራቸው እና ብቃት ያላቸው እነዚህ ተማሪዎች በመንግስት የገንዘብ በጀት ወጫቸው ተሸፍኖ ይማራሉ።

በተጨማሪም በእስትራቴጂ ደረጃ ልዩ አቅም እና ብቃት ላላቸው ተማሪዎች የእስኮላርሺፕ እድል በመስጠት ወጫቸውን እንሸፍናለን። በክፍያ ከምናስተምራቸው ተማሪዎች የሚገኘውን ገቢ በእስኮላርሺፕ የምናስተምራቸውን ተማሪዎች ወጪ እንዲሸፍን ይደረጋል።

የእስኮላርሺፕ እድል በተለያዩ ዘርፎች እንዲዳረስ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን፤ ለሴቶች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ሌሎች ዘርፎችን በማዘጋጀት ለመስጠት እንሞክራለን። የፍትሃዊነትን ጥያቄ በዚህ መንገድ ለመመለስ ጥረት ይደረጋል።

በልዩ ክፍያ ሁኔታ የሚለው ለእኛ አዲስ ነገር አይደለም፤ በራሳቸው ከፍለው የሚማሩ ተማሪዎች አሉን፣ የተለያዩ ድርጅቶች እየከፈሉላቸው የሚማሩም ተማሪዎች አሉን።  

በአሁኑ የሀገሪቱ ሁኔታ በግል ደረጃ በከፍተኛ ክፍያ የሚያስተምሩ ተቋማት አሉ። በርካታ ተማሪዎች ደግሞ የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ ከወሰዱ በኋላ በአለም አቀፍ ደረጃ ለመማር የሚሄዱ አሉ።

የተሰጠንን ራስ ገዝነት ተጠቅመን የሀገር ውስጥ አማራጭ ለመሆን እንጥራለን። የትምህርት አሰጣጣችንን በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚመደቡት የአውሮፓ እና አሜሪካ ተቋማት ጋር የሚነጻጸር ለማድረግ እንጥራለን። ዋና አላማችን አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚወስደው ክፍያ ባነሰ ለመስጠት እድል ማመቻቸት ይሆናል።  አስ

ተጨማሪ አሳይ
Back to top button