ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በአማራ ክልል ባለፉት ስምንት ወራት ከ80 በላይ ሙስሊሞች መገደላቸውን የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 1/ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል ባለፉት ስምንት ወራት፤ በመንግስትና በታጣቂ ቡድኖች መካከል እየተካሄደ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ  በሙስሊሞች ላይ እየደረሰ ባለው ጥቃት ከ80 በላይ ሰዎች መገደላቸውን፣ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ገለጸ።

የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ትላንት አመሻሽ ባወጣው መግለጫ፤ “በዋናነት በሙስሊሞች ላይ እየደረሰ ያለዉ ግፍ፣ መፈናቀል፣ ዘረፋ፣ መታገትና መገደል ከጊዜ ጊዜ እየተባባሰ ነው ” ብሏል።

መግለጫው፤ መጋቢት 29 ቀን 2016 በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 14 የመቅሪብ ሶላት ሰግደዉ ወደ ቤታቸዉ በሚሄዱ አማኞች ላይ ማንነታቸዉ ያልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች 4 የአንድ ቤተሰብ አባላትን እና አንድ ጎረቤታቸዉን በመግደል ተሰዉረዋል ብሏል፡፡

በዚያው ቀን  በሞጣ ከተማ አንድን ወጣት ካገቱ በኋላ ቤተሰቦቹን በማስፈራራት 300 ሺህ ንር ተቀብለዉ ታጋቹን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዉ ጥለዉታል ሲል የምክር ቤቱ መግለጫ አስታወቋል፡፡

በተጨማሪም በጎንደር ከተማ ማክሰኝት አካባቢ መጋቢት 28 ቀን 4 ሙስሊሞች መገደላቸውንና  በቢቸና ከተማም በቀን 26/07/2016 “ንጹሀን ባልና ሚስት ለምን ለመንግስት ግብር ከፈላችሁ” ተብለዉ በግፍ ተገድለዋል ብሏል መግለጫው፡፡

ምክር ቤቱ በአጠቃላይ በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች ባለፉት 8 ወራት ከ80 በላይ ሙስሊሞች መገደላቸውን፣ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች መፈናቀላቸውን፣ አርባ ሰባት ሰዎች መታገታቸውንና ከ260 በላይ ዘረፋዎች መፈፀማቸውን ገልጿል። 

ድርጊቶቹን በጽኑ ያወገዘው የክልሉ የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት፤ ይህንን እኩይ ተግባር ለማስቆም መንግስት፣ ሰላማዊዉ የክልሉ ህዝብ፣ የሌላ እምነት ተከታይ ወገኖች ፣ የኃይማኖት አባቶች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button