ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የህዳሴ ግድብ ድርድር ያለስምምነት መጠናቀቁን ግብጽ አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2016 .ም፡ መስከረም 12 እና 13 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሲካሄድ የነበረው የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ምንም አይነት ውጤት ሳያስገኝ ተጠናቋል ሲል የግብጽ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ኢትዮጵያ አሁንም ግትር አቋሟን እንዳንጸባረቀች ነው፣ የሚያስማማ መፍትሔ ላይ ለመድረስ ፍላጎት የላትም ብሏል።

ኢትዮጵያ በበኩሏ በዋና ተደራዳሪዋ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በኩል ባስተላለፈችው መልዕክት ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር መጠናቀቁን በመግለጽ በሀገራቱ መካከል ያሉትን ልዩነቶች ለማጥበብ ድርድርና የሃሳብ ልውውጥ ተካሂዷል፣ ኢትዮጵያ የጋራ መፍትሄ ላይ ለመድረስ በቀና መንፈስ አበክራ ትሰራለች ስትል ገልጻለች።

ኢትዮጵያ ከዚህ በፊት በተካሄዱ የሶስትዮሽ ድርድሮች ተስማምታባቸው የነበረውን ጉዳዮች በአዲስ አበባ በተካሄደው የሁለት ቀናት ድርድር ወቅት እንደ አዲስ አልስማማባቸውም ስትል ገልጻለች ሲል የግብጽ የውሃ እና መስኖ ሚኒስቴር በመግለጫው ተችቷል። ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ እንደ አዲስአልስማማባቸውም ያለችውን ጉዳዮች ዝርዝር አልገለጸም።

በቅርቡ በህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድሮች ዙሪያ ለአዲስ ስታንዳርድ አስተያየታቸውን የሰጡ ሙሁራን ከቀጣይ ድርድሮች ለውጦች ይኖራሉ ብለው እንደማይጠብቁ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል። የደቡብ ፍሎሪዳ ዩኒቨርስቲ መምህሩ እና የውሃ ባለሞያው ዶ/ር ጥሩሰው አሰፋ በበኩላቸው በግብጽ በኩል የተለየ ነገር ካልመጣ በስተቀር በቀጣይ ድርድሮች ይህ ነው የሚባል ለውጥ ይመጣል ብለው እንደማይጠብቁ ለአዲስ ስታንዳርድ አስታውቀዋል። የሃይድሮ ፖለቲክስ ተመራማሪ እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ እና አለም አቀፍ ግንኙነት የትምህርት ክፍል የሶስተኛ ዲግሪ እጩ ጋሻው አይፈራም በእኔ አረዳድ በቀጣይ የሚካሄዱ ድርድሮች ውጤት የሚያመጡ አይሆኑም ሲሉ አስተያየታቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በግብጽ ካይሮ ሲካሄድ የነበረው እና ነሃሴ 22 ቀን 2015 ዓ.ም በተጠናቀቀው የህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ያለውጤት መጠናቀቁን የግብጽ የመስኖ እና ውሃ ሀብት ሚኒስቴር ማስታወቁን አሲስ ስታንዳርድ በወቅቱ ዘግቧል። ድርድሩ ያለውጤት የተጠናቀቀው በኢትዮጵያ አሁንም ያልተቀየረ አቋም ነው ሲል ሚኒስቴሩ በመግለጫው ተችቷል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button