ዜናፖለቲካ

ዜና፡ በአማራ ክልል በመካሄድ ላይ ባለው ግጭት ሳቢያ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ከፍተኛ አደጋ ተደቅኖባቸዋል ስትል ቤተክርስቲያኗ አሳሰበች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 1/2016 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል በፌደራል መንግስቱ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በመካሄድ ላይ ያለው በከባድ መሳሪያ የታገዘ ግጭት ሳቢያ በሰሜን ወሎ ላሊበላ ከተማ የሚገኙት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በከፍተኛ አደጋ ላይ ናቸው ስትል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስታወቀች።

በላሊበላ ከተማ የሚገኙት እና በአለም ቅርስነት በዩኔስኮ የተመዘገቡት ውቅር አብያተ ክርስትያናቱ በአካባቢው በተፈጠረው ከፍተኛ የሰላም እጦትና ጦርነት ምክንያት ከፍተኛ የአደጋ ሥጋት ላይ ናቸው ሲሉ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ መናገራቸውን የቤተክርስቲያኗ የቴሌቪዥን ጣቢያ (ኢኦተቤ ቴቪ) ዘግቧል።

ብፁዕነታቸው ቅርሱ ከሥጋት ቀጠና ነጻ እንዲሆን ሁሉም አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውን የቴሌቪዥን ጣቢያው በዘገባው አስታውቋል።

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በ900 ዓመታት ውስጥ ብዙ መከራን ተሻግረዋል፣ የጣሊያን ወረራን አልፈዋል እንዲሁም በየዘመናቱ በተፈጠሩ የእርስበርስ ጦርነቶች ጉዳት ሳያደርሱባቸው እዚህ ደርሰዋል ሲሉ መናገራቸውንም አካቷል።

ብፁዕነታቸው ቅርሱ ከስጋት ነጻ ለማድረግ ይቻል ዘንድ በቅድሚያ ሁሉም አካል ወደ ሰላም መድረክ መምጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል ያለው ዘገባው ይህ ካልሆነ ግን ቅርሶቹን መጠበቅና በአካባቢው የጦርነት ድምጽ እንዳይሰማ መደረግ አለበት ማለታቸውንም አስታውቋል።

በአማራ ክልል በምትገኘው ታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ በፌደራል መንግስቱ ወታደሮች እና በፋኖ ሀይሎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ መሆኑን እና የተኩስ ድምጽ እንደሚሰማ አራት የከተማዋ ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዋቢ በማድረግ መዘገባችን ይታወሳል።

በከተማዋ ከሚገኙ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከል በአንዱ በዲያቆንነት የሚያገለግል የከተማዋ ነዋሪ በዕለቱ ከንጋቱ ሁለት ሰዓት ጀምሮ በከተማዋ ሁሉም አከባቢዎች ውጊያው መካሄድ መጀመሩን እንደገለጸለት ዘገባው አካቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ሁሉም አይነት መሳሪያዎች በውጊያው ጥቅም ላይ መዋላቸውን በመኖሪያ ቦታው ንዝረት ሳቢያ መረዳቱን እንደገለጸለትም የዜናው አውታሩ በዘገባው አስታውቋል። 

የፋኖ ሀይሎች ይዘው የነበሩትን ታሪካዊቷን ላሊበላ ከተማ ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ መከላከያ ሰራዊት ከተማዋን መቆጣጠሩን ኤኤፍፒ ነዋሪዎችን ዋቢ በማድረግ መዘገቡን ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ ም በድረገጻችን ባስነበብነው ዘገባ ተገልጿል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button