ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ በአማራ ክልል ከ100 ሺህ በላይ ህፃናት ለከፋ የምግብ እጥረት ተዳርገዋል

አዲስ አበባ፣ ጥር 4፣ 2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በተከሰተው ድርቅ ከ100 ሺህ በላይ ህፃናት ለከፋ የምግብ እጥረት መዳረጋቸውን ዶይቼ ቬሌ ዘግቧል። 

በአማራ ክልል ባለፈው የክረምት ወራት የሚጠበቀው ዝናብ ባለመጣሉ በተለይ በዋግ ኀምራ ብሔረሰብ አስተዳደር እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ውስጥ የተከሰተው አስከፊ ድርቅ በእንስሳትና በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ እንደሆነ ነዋሪዎች ተናግረዋል።  በሰሜን ጎንደር ዞን 6 ወረዳዎችና 83 ቀበሌዎች በተከሰተው ድርቅ 452 ሺህ ሰዎች ለእለት እርዳታ የተዳረጉ ሲሆን 104 ሺህ የሚሆኑት ህፃናት፣ 14 ሺህ እናቶችና ነብሰጡሮች መሆናቸውን ወረዳው አስታውቋል፡፡ 

የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር ተስፋው ባታብል በዋግ ኀምራ እና ሰሜን ጎንደር ዞኖች ከባድ ችግር መኖሩን አረጋግጠው፣ በክልሉ ከ1 ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺህ በላይ ሰዎች ለድርቅ ተጋላጭ መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ዶይቼ ቬሌ ያነጋገራቸው የሰሜን ጎንደር ዞን ጃንአሞራ ወረዳ ነዋሪዎች መንግስት በአፋጣኝና በተከታታይ እርዳታ ካላቀረበ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን አመልክተዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ድርቁ በተማሪዎች፣ በነዋሪዎችና በእንስሳት ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ ነው ብለዋል፡፡  የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳደር በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግር እርዳታ ለማድረስ እንቅፋት መፈጠሩን ነው ያመላከቱት።

ድርቁ ባሰከተለው ተጽዕኖ “ብዙ ተማሪዎች ትምህርት እያቋረጡ መሆኑ፣ እንስሳት በውሃ ጥም መደከማቸውን፣ ከ50 እስክ 60 የሚሆኑ ሰዎች በጣም ተጠቅተው አልጋ ላይ መሆናቸውን” ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። “ከሞት አድኑን፣ ድረሱልን” ሲሉም ነው ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

በወረዳው በድርቁ ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ እንስሳት ሞተዋል፣ ሌሎች ደግሞ በከፍተኛ የመኖ እጥረት ውስጥ መሆናቸውን የጃንአሞራ ወረዳ እንስሳት ሀብት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ መዲና አዳነ አመላክተዋል። እንደ ኃላፊዋ በ20 ቀበሌዎች  223ሺህ 283 የእንስሳት ሀብት ቢኖርም በድርቁ ምክንያት 10ሺህ የሚጠጋ እንስሳት ሞቷል፣ ከ115 ሺህ በላይ እንስሳት አስቸኳይ የመኖና የመድኃኒት አቅርቦት የሚፈልጉ እንደሆነም ገልጠዋል፡፡ በመሆኑም የእንስሳት መኖና መድሃኒት በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ወ/ሮ መዲና አመልክተዋል። 

የጃንአሞራ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሸጋው ተሰማ ከፌደራልና ከአማራ ክልል የተወሰነ እርዳታ ቢመጣም በቂ ባለመሆኑ ከፍተኛ የምግብና የውሀ እጥረት መኖሩን ተናግረዋል። የችግሩን ጥልቀት ለሚመለከተው እያቀረቡ ቢሆንም በቂ ምላሽ እንዳልተገኘ ነው ገለጡት፡፡ የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል ስተዳዳሪና የዞኑ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ቢምረው ካሳ ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት የተፈለገውን ያክል እርዳታ ማምጣት ባይቻልም ወደ ወረዳው የደረሰውን እርዳታ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስ እየተደረገ አንደሆነ አረጋግጠዋል፡፡ 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button