ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ መንግስት የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ከ9 ሚሊየን በላይ ተረጂዎች ድጋፍ ለማዳረስ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16/2016 ዓ.ም፡- መንግስት የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ከ9 ሚሊየን በላይ ተረጂዎች በቀጣይ ሁለት ወራት ድጋፍ ለማዳረስ እየሰራ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በበጀት አመቱ መጀመሪያ ስድስት ወራት መንግስት ከራሱ ካዝና 11 ቢሊየን ወጪ በማድረግ፤ ከለጋሽ ደርጅቶች ደግሞ 4 ቢሊየን በማሰባሰብ የ15 ቢሊየን ብር የምግብ እርዳታ ለተጎጂዎች ማከፋፈሉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎቱ ሚኒስትር ዴዔታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ ማስታወቃቸውን ፋና ዘግቧል።

በ2016 በጀት ዓመት መጀመሪያ ጀምሮ እስከ ታህሳስ ወር ድርስም ከመንግስት እና ከአጋር አካላት በተገኘ 15 ቢሊየን ብር በ3 ዙሮች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚሹ ተረጂዎች ድጋፍ እንዲያገኙ ሲሰራ ቆይቷል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታዋ መናገራቸውን ዘገባው አመላክቷል።

በዚህም በመጀመሪያ ዙር ለ7 ነጥብ 3 ሚሊየን ወገኖች፣ በ2ኛው ዙር ለ3 ነጥብ 6 ሚሊየን ወገኖች በሶስተኛው ዙር ደግሞ ለ6 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረስ ተችሏል ማለታቸውንም ዘገባው አካቷል።

በጥሬ ገንዘብም ድጋፍ መደረጉን ሚኒስትር ዴዔታዋ ተናግረዋል ያለው ዘገባው የአካባቢው ገበያ ተጠንቶ በአካባቢያቸው ያለውን ምግብ ገዝተው እንዲጠቀሙ 2 ቢሊየን ብር ድጋፍ ተደርጓል ማለታቸውን አስታውቋል።

በጥሬ ገንዘብ የተሰራጨው ብርም በአማራ ፣ኦሮሚያ፣ ሶማሌ ፣ ትግራይ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ አፋር እና ሐረሪ ክልሎች የተደረገ መሆኑን ተናግረዋል ያለው ዘገባው የተሰራጨውን የጥሬ ብር ድጋፍ 40 በመቶ መንግስት እንዲሁም 60 በመቶው ቀጥታ ከዓለም ባንክ የተገኘ መሆኑን ጠቁመዋል ብሏል፡፡

በቀጣይም በድርቅ እና በተለያዩ ምክንያቶች ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ከ9 ሚሊየን በላይ ወገኖች ተለይተው እርዳታውን ከጥር እስከ የካቲት ለማድረስ እየተሰራ ነው ማለታቸውንም አስታውቋል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ለነዚህ ወገኖች የሚደርሰውን እርዳታ የማሰባሰብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም 9 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button