ዜና

ዜና፡ በኦሮሚያ ክልል የተጠራው የትራንስፖርት እንቅስቃሴና የንግድ ክልከላ በተወሰነ መለኩ ተግባራዊ መደረጉን ነዋሪዎች ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21/ 2016 ዓ/ም፦ በኦሮሚያ ክልል ለሁለተኛ ጊዜ የተጠራውን የትራንስፖርት እንቀሰቃሴ እና የንግድ ክልከላን ተከትሎ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በተወሰነ መለኩ ተግባራዊ መደረጋቸውን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ገለጹ።

ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለገ የሆሮ ጉዱሮ ወለጋ ዞን ሻምቡ ከተማ ነዋሪ እንደገለጸው፤ ከትላንት ጥር 20 ጀምሮ በዞኑ በርካታ አካባቢዎች የተራንስፖርት እና የንግድ እንቅስቃሴዎች ተገድቧል። 

“በሻምቡ ከተማ የተሽከርካሪዎችም ሆነ የሰዎች እንቀሰቃሴዎች ብዙ የለም። በትላንተናው እለት ባንኮችን ጨምሮ ድርጅቶች መደበኛ ስራቸውን አቋረጠው ነበር። የመንግስት አካሎች በከተማዋ ውስጥ በመንቀሳቀስ የተዘጉ የንግድ ቤቶችን ሲያሽጉ ነበር” ብሏል። ክልከላው ከትላንት ጀምሮ ተግባራዊ እየሆነ ነው ያለው ነዋሪው መች አንዲሚያበቃ ግን አይታወቅም ብሏል። 

የነቀምት ከተማ ነዋሪ ትላንት የትራንስፖርት እንቀስቃሴ እና የንግድ ክንውኖች መቋረጣቸውን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል። በኋላ ላይ ግን የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች በሰጡት ማስጠንቀቂያ በዛሬው ዕለት ባጃጆች እንቀስቃሴ መጀመራቸውን እና የንግድ ቤቶችም እየተከፈቱ መሆኑን ተናግሯል። 

ስሙ እንዳይጠቀስ የጠየቀ አንደ የመቂ ከተማ ነዋሪ በከተማዋ እና በአካባቢው የትራንስፖርት እንቅስቃሴ እና የንግድ ስራዎች የተገደቡ መሆናቸውን ገልጿል።

የኦሮሚያ አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ የተጠራውን ክልከላ አስመልክቶ ትላንት ምሽት ባወጣው መግለጫ “በክልሉ የትራንፖርት አገልግሎት እና የንግድ ስራን በማደናቀፍ ህዝቡን ለማመረር ሙከራ መደረጉን” ገልጾ ይህን ያቀነባበረውም “ሸኔ” ነው ብሏል። 

በምስራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉዱሮ ወለጋ፣ ምዕራብ ወለጋ እና ምዕራብ ሸዋ ወረዳዎች እንዲሁም በነቀምት ከተማ በተወሰኑ አካባቢዎች “ጠላት” ያላቸው አካላት “በማህበራዊ ሚዲያ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የልማት እንቅስቃሴዎችን ለማደናቀፍ ሞክሯል” ያለው መግለጫው፤ ይሁን እንጂ “የመንግስት አካላት እና የጸጥታ ኃይሎች መውሰደ በጀመሩት እርምጃ በአሁኑ ሰዓት በአንዳድ አካባቢዎች ህብረተሰቡ አንቅስቃሴ እና ስራውን ጀምሯል” ሲል ገልጿል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

እገዳውን የጠራው መንግስት “ሸኔ” እያለ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን መሆኑ እየገለጽ ሲሆን አዲስ ስታንዳርድ ጉዳዩን በተመለከተ ስሙ እየተነሳ ካለው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ለማረጋገጥ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። 

አሁን በተወሰነ መልኩ እየተከናወነ ያለው የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እና የንግድ አድማ ተግባራዊ ሲሆን ለሁለተኛ ግዜ ሲሆን በተመሳሳይ መልኩ ከሳምንታት በፊፍ የተጠራውን የትራንስፖርት አንቀሰቃሴ ክልከላ የተላለፉ ተሽከርካሪዎች ላይ በተወሰደ እርምጃ በተለያዩ አካባቢዎች የንብረት ውድመት ማደረሱ  መዘገቡ ይታወቃል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button