ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ በ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ለአማራ ክልል አርሶአደሮች በወቅቱ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17/2016 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል የ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት ጉዳዮች ላይ የፌደራል እና የክልል የስራ ሃላፊዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት መካሄዱ ተጠቆመ።

የመድረኩም ዓላማ ቀጣይ የስራ አቅጣጫዎች ላይ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ መሆኑን በመግለጽ ለአርሶአደሩ የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ማድረስ እንደሚገባ የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ መናገራቸውን ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው የ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለአርሶአደሩ ለማድረስ በፌደራል መንግስት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ማብራራታቸውንም ሚኒስቴሩ በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ የፌስቡክ ገጹ ያጋራው መረጃ ያሳያል።

የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ተፈፅሞ በአግባቡ ተጓጉዞ በወቅቱ ከአርሶአደሩ እንዲደርስ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል ያለው የሚኒሰቴሩ መረጃ የኢንቨስትመንት እና ግብይት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) የአማራ ክልል የ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ስርጭት የአፈፃፀም ሪፖርት ማቅረባቸውን ጠቁሟል።

የአፈር ማዳበሪያ ግዢ ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎች፣ የምርት ዘመኑ የማዳበሪያ አቅርቦት ያለበት ደረጃ፣ የአቅርቦት አፈጻጸም፣ በአቅርቦት ሂደት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እና መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮች በሪፖርቱ መመላከታቸውን አስታውቋል፡፡

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button