ዜናቢዝነስ

ዜና፡ ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ማዳበሪያ ለማቅረብ እና በሀገር ውስጥ ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ የሁለትዮሽ ውይይት አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ጥር 24/2016 ዓ.ም፡- የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ እና የግብርና ሚኒስትር ዴኤታዋ ዶ/ር ሶፊያ ካሳ በሩሲያ የኢንዱስትሪና ንግድ ምክትል ሚኒስትር ሚካሂል ዩሪን የተመራ ልዑካን ቡድን ተቀብለው ማነጋገራቸው ተገለጸ።

ልዑካን ቡድኑ ሩሲያ ማደበሪያ ለኢትዮጵያ ማቅረብ በምትችልበትና ማዳበሪያው በኢትዮጵያ ማምረት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጉን ከግብርና ሚኒስቴር ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ኢትዮጵያ በግብርና ሜካናዜሽን እና ማዳበሪያ ማምረቻ ዘርፍ ከሩሲያ ልታገኝ ከምትችለው ልምድና የቴክኖሎጂ ድጋፍ አኳያ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል መባሉን የጠቆመው መረጃው የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ ሩሲያ የማዳበሪያ ግብዓትን ለማሟላት ብሎም ለማምረት እያደረገች ያለውን ትብብር ማድነቃቸውን አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችሉ እና ያሉትን ምቹ ሁኔታዎች አስመልክተው ሚኒስትሩ ለሉዑካኑ ማብራሪያ መስጠታቸውን የጠቆመው መረጃው በሁለትዮሽ ውይይቱ የሁለቱ አገራት የማዳበሪያ ግብዓት አሁናዊ ቁመና ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ብሏል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ሶፊያ ካሳ በኢትዮጵያ ጥቅም ላይ የሚውለውን የዩሪያ ማዳበሪያ ዓይነት፣ ዝርዝር መግለጫ፣ የኬሚካል መስፈርቶች እና የሄቪ ሜታል ብክለት ገደቦችን ማቅረባቸውን ያስታወቀው የሚኒስቴሩ መረጃ በሩሲያ ኩባንያ የቀረበው ዩሪያ ዓይነት እና ዝርዝር ተመሳሳይ ቢሆንም ከኢትዮጵያ በኩል የሚፈለጉትን መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ ለማሟላት አንዳንድ ቴክኒካል ማስተካከያዎች እንደሚያስፈልጋቸው ሚኒስትር ዴኤታዋ መናገራቸውን አመላክቷል።

የሩሲያ የኢንዱስትሪና ንግድ ምክትል ሚኒስትር ሚካሂል ዩሪን በበኩላቸው ማዳበሪያ በማቅረብና በማምረት ሂደት ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጎን መሆኗን ገልጸው ሩሲያ ግዙፍ የማዳበሪያ አምራች መሆኗን በመጠቆም ለኢትዮጵያ ማዳበሪያ የማቅረብና የማምረቱን ተግባር ከዳር ለማድረስ ሁለቱ አገራት ጠንክረው ሊሰሩ ይገባል ማለታቸውንም አስታውቋል።

ለዚሁ ተግባር የቴክኒክ ቡድን ተቋቁሞ እስከ ሚዚያ 2016 ድረስ ዝርዝር ተግባራት ተሰርተው እንዲቀርቡ ዶ/ር ግርማ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን የሚኒስቴሩ ይፋዊ መረጃ ያሳያል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button