ዜናቢዝነስ

ዜና፡ ኢትዮጵያ የውጭ እዳ መክፈል ከተሳናቸው ሀገራት ተርታ ተመድባለች ተባለ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16/2016 .ም፡ ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ ገበያ የሸጠችው የአንድ ቢሊዮን ዶላር ቦንድ አከፋፈል ላይ ከአበዳሪዎቿ ጋር ያደረገችው ድርድር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ የውጭ ዕዳዋን መክፈል የማትችልበት ደረጃ (ዲፎልት) ላይ እንደምትገኝ ብሉንበርግ በዘገባው አስታወቀ።

ኢትዮጵያ እዳ መክፈል ከተሳናቸው ሀገራት ዛምብያ፣ ሲሪላንካ እና ጋና ተርታ ተመድባለች ብሏል።

ኢትዮጵያ ለአበዳሪዎቿ ታህሳስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም መክፈል የሚጠበቅባትን 33 ሚሊየን ዶላር ወለድ መክፈል እንደማትችል መግለጿን ተከትሎ 14 ቀናት የእፎይታ ግዜ የነበራት ሲሆን ይህም የእፎይታ ግዜ ትላንት ታህሳስ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ተጠናቋል።

በዚህም ሳቢያ ኢትዮጵያ የውጭ ዕዳዋን ለአበዳሪዎቿ መክፈል የማትችልበት ደረጃ (ዲፎልት) ላይ እንደምትገኝ በዘገባው አስታውቋል።

መንግስ ለአበዳሪዎች መክፈል የሚጠበቅበትን 33 ሚሊየን ዶላር ያልከፈለው ሁሉንም አበዳሪዎቹን እኩል ለማስተናገድ እንጂ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ጋር በተያያዘ አይደለም ሲል በገንዘብ ሚኒስትሩ በኩል በብሔራዊ ቴሌቪዥን ኢቲቪ መግለጹ ይታወሳል።

ከቀናት በፊት ሮይተርስ የዜና ወኪል በገንዘብ ሚኒስቴር ባለስልጣናት እና በቦንድ አበዳሪዎች መካከል ታህሳስ 4 ቀን 2016 ዓ.ም በተካሄደው ውይይት ወቅት ተሳታፊ ከነበሩ ሶስት ሰዎች ሰማሁ ብሎ ባቀረበው ዘገባ የኢትዮጵያ መንግስት ለአበዳሪዎቹ አዲስ ውል ማዘጋጀቱን እና በውሉም አበዳሪዎቹ የሚያጋጥማቸውን ኪሳራ የሚያካክስ ሀሳብ ማካተቷን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ በውይይቱ ለአበዳሪዎቿ ያቀረበችው የመፍትሄ ሀሳብ በቀደመው ሳምንት ለዋና ዋና የቦንድ ገዢዎች ቡድን አቅርባ ውድቅ ከተደረገባት ሀሳብ ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ውይይቱን ከተካፈሉ ሰዎች መስማቱን ሮይተርስ በዘገባው ጠቁሟል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button