ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ ለደንብ ልብስ ግዢ በሚል ያከናወነው ክፍያ የተጋነነ መሆኑ የተነገረው #የቱሪዝም ሚኒስቴር በተጋነነ ዋጋ ከሚያከናውነው ግዢ መታረም እንዳለበት ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 18/2016 .ም፡ የቱሪዝም ሚኒስቴር በተጋነነ ዋጋ የሚያከናውነው ግዢ መታረም እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የመንግስትን የፋይናንስ ስርዓት በመጣስ የተለያዩ ስህተቶችን መፈጸሙን ቋሚ ኮሚቴው የቱሪዝም ሚኒስቴርን የ2014 በጀት ዓመት ሂሳብ ኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ ባካሄደው ይፋዊ የውይይት መድረክ መገለጹን ከምክር ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለደንብ ልብስ ግዢ በሚል ያከናወነው ክፍያ የተጋነነ መሆኑን በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ተናግረዋል ያለው መረጃው በቀጣይ የቱሪዝም ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች ተቋማት የሚመሩበት ወጥ የሆነ መመሪያ በገንዘብ ሚንስቴር ሊዘጋጅ እንደሚገባ ማሳሰባቸውንም አስታውቋል።

በተቋሙ የፋይናንስ ዘርፍ ያሉት ክፍተቶች ተፈትሸው ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ ከተቋሙ የለቀቁ ሰራተኞች የተቋሙን ንብረት ተመላሽ እንዲያደርጉ እንዲሁም ያለአግባብ ለቤት እድሳት የወጣው ገንዘብ ተመላሽ እንዲደረግ ቋሚ ኮሚቴው ለሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ያስቀመጣቸው አቅጣጫዎች መሆናቸውንም አመላክቷል።

ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ የቀረበበትን የኦዲት ግኝት መነሻ በማድረግ የእርምት እርምጃ መውሰድ የሚያስችለውን የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ እስከ ታህሳስ 25/2016 ዓ.ም ድረስ እንዲያቀርብ አቅጣጫ መሰጠቱንም ጠቁሟል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው በተቋሙ በየቀኑ ነዳጅ የሚሞላላቸው ተሸከርካሪዎች እንዲሁም ያለአግባብ የተከፈሉ ወጪዎች መኖራቸው በኦዲት ግኝት እንደተረጋገጠ ገልጸው፤ ተቋሙ የእርምት እርምጃ አልወሰደም ሲሉ አስታውቀዋል።

የቱሪዝም ሚንስቴር ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በበኩላቸው ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርብ የተቋቋመና ቀደም ሲል በድጎማ በጀት የሚተዳደር እንደመሆኑ የተለያዩ የአሰራር ክፍተቶች እንደነበሩበት አስረድተዋል ያለው ምክር ቤቱ ተቋሙ የውስጥ ኦዲት፣ የስነምግባር፣ የፋይናንስ፣ የንብረትና የተለያዩ ክፍሎችን በአዲስ መልክ በማደራጀትና ለባለሙያዎች ስልጠና በመስጠ ቀደም ሲል የነበሩት የኦዲት ግኝቶች እንዳይደገሙ ውጤታማ ስራዎች እየሰራ ይገኛል ማለታቸውንም አካቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button