ዜናጤና

ዜና፡ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያግዝ አንድ ሚሊየን ዩሮ ለገሰ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30/2016 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመከላከል የሚያግዝ አንድ ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ መስጠቱን የአውሮፓ ህብረት አስታወቀ። በሀገሪቱ የኮሌራ ወረርሽኝ የተከሰተው ከነሃሴ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑ ይታወቃል።

እገዛው የተሰጠው ድንገተኛ የኮሌራ ወረርሽኞችን ለመከላከል መሆኑም ተጠቁሟል። በዛሬው ዕለት ጥቅምት 30 2016 ከተሰጠው ልገሳ በተጨማሪ ህብረቱ በኮሌራ ወረርሽኝ የተጠቁ የማህበረሰብ ክፍሎችን የሰብአዊ ዕርዳታ እያቀረበ እንደሚገኝ ተገልጿል።   

በሀገሪቱ የተመዘገበ ይፋ መረጃ እንደሚያሳየው የኮሌራ ወረርሽኝ ከተከሰተበት እለት ጀምሮ 26ሺ ተጠቂዎች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም 370 የሚሆኑት ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።

የኮሌራ ወረርሽኙ ከተነሳባቸው አከባቢዎች መካከል በተፈጥሮ መዛባት እና በግጭት ሳቢያ ከቀያቸው ተፈናቅለው በመጠለያ በሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎች ጭምር መሆኑም ተጠቁሟል።

የአውሮፓ ህብረት በግጭቶች እና በተፈጥሮ ሳቢያ ተጎጂ ለሆኑ ኢትዮጵያውያን እገዛ የሚውል 82 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ በ2023 ለማድረግ መመደቡ ይታወሳል።

ባሳለፍነው አመት 2015 ግንቦት ወር ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ኦቻ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያመለክተው ሰባት ሚሊየን ኢትዮጵያውያን የኮሌራ ወረርሽኝ ሊያጠቃቸው ይችላል ሲል ስጋቱን መግለጹን መዘገባችን ይታወሳል።

 የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ እንዳስታወቀው ኢትዮጵያ የአሁኑ አይነት ለበርካታ ወራት የቆየ እና በታሪኳ የተመዘገበ የኮሌራ ወረርሽኝ አይታወቅም፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተከሰተው የኮሌራ ወረርሽኝ የተመዘገበው በነሃሴ ወር 2014 እንደነበር አውስቷል።  በሚያዚያ 2023 አንድ ነጥብ ዘጠኝ ሚሊየን የኮሌራ ክትባት በመላ ሀገሪቱ መሰራጨቱን ሪፖርቱ አመላክቷል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ኦቻ ለኮሌራ ወረርሽኙ እየሰጠ ያለው ምላሽ በበቂ ፈንድ እጥረት፣ ውስን አጋሮች ብቻ መኖር እና ተያያዥ ጉዳዮች እንቅፋት እንደሆኑበት እና በሚገባ እንዳያከናውን እንዳደረጉት በወቅቱ በሪፖርቱ አስታውቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button