ዜናፖለቲካ

ዜና፡ የኢትዮጵያ እና የኬንያ የደኅንነት ተቋማት ቀጣናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን የመረጃ ልውውጥና የጋራ ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 17/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ እና የኬንያ የደኅንነት ተቋማት ቀጣናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን የመረጃ ልውውጥና የጋራ ኦፕሬሽን አጠናክረው ለመቀጠል መስማማታቸው ተገለጸ።

የኬንያ ናሽናል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ኖርዲ ሐጂ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ትላንት ጥር 16 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱም የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል ተመስገን ጥሩነህና ሌሎች የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች አቀባበል እንዳደረጉላቸው ፋና በዘገባው አስታውቋል።

የኢትዮጵያና የኬንያ የመረጃና የደኅንነት ተቋማት በወቅታዊና ቀጣናዊ ጉዳዮች መምከራቸውን የጠቆመው ዘገባው የኢትዮጵያና የኬንያ አቻ ተቋማት ጠንካራ ትብብር እንዳላቸውና ይህንንም አስጠብቀው መዝለቃቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት መግለጻቸወን አስታውቋል።

ተቋማትቱም በመረጃ ልውውጥና በተለያዩ መስኮች የሚያደርጉትን ትብብር በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል ቁርጥኝነት መኖሩን የገለጹት አቶ ተመስገን÷ በዚህም በቀጣናው የሚገኙ ሀገራትን ጥቅም ያማከሉ የአጋርነት ማዕቀፎች የትኩረት ማዕከል እንደሚሆኑ አስታውቀዋል ብሏል፡፡

አቻ ተቋማቱ በድንበር ተሸጋሪ ወንጀሎች፣ በአቅም ግንባታ መስኮች፣ በሕገወጥ የጦር መሣሪያና የሰዎች ዝውውር ዙሪያ መረጃዎችን በመለዋወጥና የጋራ ኦፕሬሽኖችን በማካሄድ ቀጣናዊ ሰላምንና ደኅንነትን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትብብር ለመሥራት መስማማታቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ መረጃዎችን ከመለዋወጥና የጋራ ኦፕሬሽኖችን ከመምራት ባሻገር ወቅታዊ የሥጋት ምንጮችን በመለየት ተሞክሮዎችን ለመጋራትና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት በላቀ ደረጃ እንደሚጠናከሩ አስታውቀዋል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የሀገራቱ የመረጃና የደኅንነት ተቋማት ሽብርተኝነትንና ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የተቀናጀ ስምሪት እያካሄዱ መሆናቸውን የኬንያ ናሽናል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ ዳይሬክተር ጀነራል ኖርዲ ሐጂ ገልጸዋል ያለው ዘገባው በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚታዩ የደኅንነት ሥጋቶችን ለመከላከል የሁለቱ ሀገራት ትብብርና ጥምረት ወሳኝ ሚና እንዳለው ማወሳታቸውን አመላክቷል።

በተለይ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ያላትን ውጤታማ ተሞክሮ እንደ ግብዓት በመውሰድ የመረጃ ልውውጥና የጋራ ኦፕሬሽኖች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል ያለው የፋና ዘገባ በቀጣናው የሚታዩ የደኅንነት ሥጋቶችን አስቀድሞ በማወቅ ለመከላከል የሚከናወኑ ቅንጅታዊ ሥምሪቶች የጋራ ጥቅምን ለማስጠበቅ ጉልህ ሚና እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button