ዜናጤና

ዜና፡ ጥራቱ ተረጋግጦና ህጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶት ለገበያ የቀረበ ባህላዊ መድኃኒት የለም ሲል #የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለሥልጣን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 24/2016 ዓ.ም፡- ጥራቱና ፈዋሽነቱ ተረጋግጦ ለገበያ የቀረበ ባህላዊ መድኃኒት ባለመኖሩ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ማስታወቁን ኢፕድ ዘግቧል።

በማህበራዊ ሚዲያ ሃሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ቢበራከቱም ጥራቱ ተረጋግጦና ሕጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶት ለገበያ የቀረበ ባህላዊ መድኃኒት የለም ሲሉ በባለሥልጣኑ የመድኃኒት ምዝገባና ፈቃድ ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ በየነ መግለጻቸውን ዘገባው አመላክቷል። በመሆኑም ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ማለታቸውንም አካቷል።

በኢትዮጵያ የባህላዊ መድኃኒት አዋቂዎች በየአካባቢያቸው ከሚቀምሙት መድኃኒት በሳይንሳዊ መንገድ ተረጋግጦና ተመርቶ ለገበያ የዋለ መድኃኒት የለም ማለታቸውን ያስታወቀው ዘገባው ባለሥልጣኑ ባህላዊም ሆነ ዘመናዊ መድኃኒቶች ተመዝግበው ገበያ ላይ እንዲውሉና ሕዝብ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ እየሠራ ነው ማለታቸውንም ጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት ባህላዊ መድኃኒት ላይ የተሰማሩ ሰዎች የሚቀምሙት መድኃኒት በባለሥልጣኑ ተመዝግቦ ወደ ገበያ እንዲገቡ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው የትኛውም መድኃኒት ወደ ገበያ ከመቅረቡ በፊት በትክክለኛው የሕክምና ሰውና በመሳሪያ መፈተሽ እንዳለበት አመላክተው፤ የንጥረ ነገሮቹ ይዘት፣ ለየትኛው በሽታ ፈዋሽ እንደሆነና የጎንዮሽ ጉዳቱ በላብራቶሪ ፍተሻ መረጋገጥ እንዳለበት አስረድተዋል ብሏል።

አብዛኛው ባህላዊ መድኃኒት በኢትዮጵያ የሚገኙ የባህል መድኃኒት አዋቂዎች የመጀመሪያው የመድኃኒት የዝግጅት ደረጃ በሆነው ተክሎችንና የተለያዩ ግብዓቶችን በማድረቅ፣ በዱቄትና በሚበጠበጥ መልኩ እንደሚያዘጋጁ ጠቅሰው፤ ወደ ተሻለው በክኒንና ፈሳሽ መልክ የማዘጋጀት ደረጃ ላይ አለመድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡

በርካታ ባህላዊ መድኃኒቶች በምርምር ደረጃ ላይ መሆናቸውን አመላክተው፤ ጥናትና ምርምር የተደረገባቸው መድኃኒቶች ወደ ምርት የመቀየር ሥራዎች እየተጠበቁ መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡

ባህላዊ መድኃኒት አዋቂዎች የቀመሟቸውን መድኃኒቶች ደህንነት፣ ፈዋሽነትና ጥራት ማረጋገጥ እንደሚገባ በተለያዩ መድረኮች ላይ ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button