አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 29/2016 ዓ.ም፡– በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት በዲጂታል የባንክ አገልግሎት የ2 ነጥብ 8 ትሪሊየን ብር ዝውውር መፈፀሙን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በይፋዊ የማህበራዊ ሚዲያ የፌስቡክ ገጹ ባጋራው መረጃ አስታወቀ።
በዲጂታል የባንክ አገልግሎት አማራጮች ከ494 ሚሊዮን በላይ ግብይቶች መከናወናቸውንም የባንኩ የዲጂታል ባንክ ዲቪዠን የመርቻንት እና ኤጀንት ባንኪንግ ዳይሬክተር አቶ ብሌን ሀ/ሚካኤል መናገራቸውን መረጃው ጠቁሟል።
የስድስት ወራቱ አፈጻጸም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በግበይት ብዛት የ35 በመቶ እንዲሁም በገንዘብ መጠን የ118 በመቶ እድገት ማሳየቱንም ባንኩ አመላክቷል።
ዲጂታል አማራጮችን የሚጠቀሙ ደንበኞች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን አቶ ብሌን ገልጸዋል ያለው መረጃው ባንኩ በአሁኑ ጊዜ ከ12 ሚሊዮን በላይ የኤ.ቲ.ኤም ካርድ ተጠቃሚዎች፣ ከ9 ሚሊዮን በላይ የሞባይል ባንኪንግና ከ20 ሚሊዮን በላይ የሲቢኢ ብር ተጠቃሚ ደንበኞች እንዳሉት መናገራቸውንም አካቷል።
አቶ ብሌን ባንኩ አዳዲስ ዲጅታል የክፍያ አገልግሎቶት አማራጮችን በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ጨምረው መግለጻቸውም በመረጃው ተጠቁሟል።