ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ መንግስት በዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች የድመወዝ መዘግየትና ያለመከፈል ችግርን እንዲቀርፍ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 17/2016 ዓ/ም፦ በድቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች የድመወዝ መዘግየት እና ያለመከፈል ችግር እንዲቀረፍ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የፌደራል፣ የክልሉን እና የዞኑን መንግስትን ጠየቀ።

የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ዛሬ ሚያዚያ 17 ቀን 2016 ዓ/ም ባወጣው መግለጫ በዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች ጋር ባደረገው ስብሰባ፤ ከደመወዝ ጋር የተያያዙ ችግሮች ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሚስተዋሉ መሆኑንና ላልፉት ሰባት ወራት በየወሩ መጨረሻ ሊከፈለ የሚገባው ደመወዝ ከ10 እስከ 20 ቀን እንደሚዘገይ መረዳቱን ገልጿል።

ከመስከረመ ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ እስከ የካቲት ወር 2016 ዓ.ም በየወሩ መጨረሻ መከፈል የሚገባው ድመወዝ አንድ ሶስተኛ በመቆራረጥ በሶስት ዙር ሲሰጥ መቆየቱን የገለጸው ንቅናቄው፤ የየካቲት ወር 2016 ደመወዝ 80 በመቶ ብቻ መከፈሉን ገልጿል።

በተጨማሪም፤ ከሶዶ ከተማ ሠራተኞች በስተቀር በሁለም የመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች ደመወዝ ከመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሚያዚያ 15 ቀን 2016 ድረስ “ሙለ በሙለ” መቋረቱን አስታውቋል። 

በዚህም ምክያት ሠራተኞች ለዘርፈ ብዙ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሥነ-ሌቦናዊ ቀውስ ተጋልጠዋል ሲል የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ በመግልጫው አስገንዝቧል።

ተገቢውን ደመወዝ በወቅቱ አለመክፈል የሥራ መብት ጥሰት ከመሆኑም በተጨማሪ ሌሎች የአለም አቀፍ የኢኮኖሚያዊ፣ የማኅበራዊ እና የባህላዊ መብቶች ቃልኪዳን ውስጥ ጥበቃ ያገኙ መብቶች ጭምር  በፌደራል እና በክልሉ መንግስት ተጥሰዋል ሲል ከሷል።

የጤና መብት ጋር በተያያዘ በዞኑ የከተማና ወረዳ አስተዳደሮች ውስጥ የሚገኙ ጤና ጣቢያዎች እና ጤና ኬላዎች ተግቢውን አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑ በተለይም በግለ የጤና ተቋማት መታከም አቅም የሌላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች በከፋ የጤና ችግር ውስጥ ይገኛሉ ሲል ገልጿል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተጨማሪም ፓርቲው፤ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከሚያዚያ ወር መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ከ70በመቶ በላይ የመማር ማስተማር ስራ ተቋርጧል ብሏል።

ሠራተኞቹ ደመወዝ በመቋረጡ ምክንያትና ሌላ ገቢ የሌላቸው በመሆኑ ራሳቸው እና የቤተሰቦቻቸው የዕለት ጉርስ ለማግኘት፣ የቤት ኪራይ ለመክፈል  እየተቸገሩ ነው ያለው መግለጫው፤ ህይወታቸውን ለማቆየት የቤት እቃ በመሸጥ ሊይ ይገኛለ ሲል ገልጿል። 

የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ የፌደራል መንግሥት፣ የክልሉ እና የዞኑ የመንግሥት አፋጣኝ መፍትሔ እርምጃዎችን በመውሰድ የሠራተኞች ደመወዝ ወቅቱን ጠብቆ መከፈለን እና ሰብአዊ መብቶቹ መከበራቸውንና መጠበቃቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርቧል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ መም/ራን ማህበር፣ የደቡብ ኢትዮጵያ መም/ራን ማህበር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዎላይታ ዞን የሚታየው የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ ክፍያ ችግር፣ የሥራ መብት፣ የመንግስት ሰራተኛ በቂ የኑሮ ደረጃ የማግኘት መብት፣ የመማር መብትንና የጤና መብት ጥሰትን እንዲያጣሩ እና የመፍትሔ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል። አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button