ዜናማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በዋግ ኽምራ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት በሰሃላ ወረዳ የ6 ሰዎች ህይወት በርሃብ አለፈ፤ ድርቁ የእንስሳትንም ህይወት እየቀጠፍ ነው 

አዲስ አበባ፣ ህዳር 7/2016 ዓ/ም፦ በአማራ ክልል በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር በተከሰተው ድርቅ በርሃብ ብቻ የስድስት ሰዎች ህይወት ማለፉን የዞኑ የምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ፅ/ቤት ለአዲስ ስታንዳርድ አስታወቀ፡፡ 

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ፅ/ቤቱ ሃላፊ አቶ ምረት መላኩ በዞኑ የተከሰተው ድርቅ በተለይ በሰሃላ ወረዳ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱንና የዘንድሮ የሰብል ምርት ሙሉ ለሙሉ መውደሙን ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጸዋል፡፡

በክልሉ ባለው ግጭት መንገዶች መዘጋታቸው ክፍተኛ ተጽእኖ መፍጠሩን የጠቀሱት የፅ/ቤት ሃላፊ ቀደም ሲል ለእርዳታ ለሚውል 230 ኩንታል ሰንዴ “ኢ-መደበኛ” ሲሉ በጠሩዋቸው ሃይሎች መዘርፉን አስታውሰዋል፡፡

እንደ ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ  አስተዳደር ኮሚዩኒኬሽን ዘገባ በሰሃላ ወረዳ ከ2015 ለ 2016 ዓ.ም በተከሰተው የተፈጥሮ ድርቅ የሰውና የእንስሳት ህይወት እየተቀጠፈ መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ ብሩ አረጋግጠዋል፡፡ በወረዳው አስተዳደር እጥረትና ርሃብ ምክንያት የ6 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና በመኖ እጥረት 4ሺ 600 እንስሳት መሞታቸውን ገልጸዋል፡፡

አስተዳዳው በወረዳው ከሚገኘው 51 ሺ በላይ ህዝብ ውስጥ 46 ሺህ የሚሆነው አስቸኳይ የህይወት አድን ርደታ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። 

የዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር የምግብ ዋስትናና አደጋ መከላከል ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ምረት መላኩ በብሄረሰብ አስተዳደሩ በሚገኙ ሶስት ቆላማ ወረዳዎች ላይ 26 ቀበሌዎች በተፈጥሮ ድርቅ አደጋ መጋለጣቸውን ገልጸው፤ በስሃላ፣ ዝቋላና አብርገሌ ወረዳዎች ውስጥ ድርቁ በመከሰቱ የሰውና እንስሳት ህይወት እየቀጠፈ ነው ብለዋል። ከ180 ሺ በላይ ህዝብ በድርቁ ህይወታቸው አደጋ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሰሃላ ወረዳ የ09 ቀበሌ ነዋሪዎች በተከሰተው ድርቅ ህፃናት ልጆቻቸውን መቀለብ እንደተሳናቸው የዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ዘግቧል። የቀበሌው ነዋሪ ወይዘሮ ፍትጌ ዘሪሁን በተከሰተው ድርቅ የዘሩት ሰብል አፈር በልቶት በመቅረቱ ለርሃብ ተጋልጫለሁ ብለዋል፡፡ 5 ልጆቼን አብልቼ የማስተዳድርበት አቅም ስላጠረኝ ችግር ላይ በመሆኔ መንግስት በአስቸኳይ ድጋፍ እንዲያደርግልን ስትል ጠይቃለች።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

በተመሳሳይ የቀበሌው ነዋሪ አቶ ጥፍጤ ክንፉ የዘሯቸው ሰብሎች ሳይበቅሉ  በመቅረቱ ለችግር መጋለጣቸውንና በርሀብ ምክንያት “ቁርባ” የሚባል ህመም እየታመሙ መሆኑን  ገልጸዋል። 

የሰሃላ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሲሳይ እስካሁን የተደረጉ ድጋፎች ቢኖሩም ከችግሩ ስፋት አንጻር አጥጋቢ አለመሆኑንም አክለው ተናግረዋል። በመሆኑም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህንን ህዝብ ከተጋረጠበት የርሃብ አደጋ ለመታደግ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ምረት መላኩ በበኩላቸው በመጀመሪያ ዙር በተደረገ የምግብ እህል ድጋፍ 8 ሺ 684 ኩንታል በማሰባሰብ ለ34 ሺ ሰዎች የእለት ድጋፍ ቢደረግላቸውም  በቂ አለመሆኑን ገልጸዋል።

“ድርቅ የተከሰተባቸው ወረዳዎች ከፍተኛ የእንስሳት እርባታ ያለባቸው ቢሆንም በተከሰተው ድርቅ የእንሰሳት ህይወት አልፏል። እያደረሰ ያለው ኪሳራም ትልቅ ነው፤ በቀጣይ የሰውም ሆነ የእንስሳት  ህይወት እንዳይጠፋ ተጋግዘን እንድናልፍ ሁሉም ሰው የበኩሉን  ድርሻ ይወጣ” ሲሉ  ጠይቀዋል።

መስከረም ወር በክልሉ በዋግ ኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ሰሀላ ሰዬምት ወረዳ በተከሰተ ድርቅ የሁለት ሰዎች ህይወት ማለፉና በተመሳሳይ መልኩ በሰሜን ጎንድር ዞኖች በተከሰተ ድርቅ በጃናሞራ ወረዳ 16 ሰዎች በረሃብ ምክንያት መሞታቸውን አዲስ ስታንዳርድ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button