ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና: በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከ84 በላይ ተንጠልጣይ ድልድዮች እንደሚገነቡ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13/2016 ዓ.ም፡- በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከ84 በላይ ተንጠልጣይ ድልድዮች እንደሚገነቡ የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ሃላፊው ይህንን ያስታወቁት ሄልቬታስ ኢትዮጵያ እና ብሪጅስ ቱ ፕሮስፐሪቲ የተንጠልጣይ ድልድይ ቴክኖሎጂ ግንባታ እና ጥገና በቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች ሥልጠና በማስጀመር ሥነ ሥርዓት ላይ ነው።

ሥልጠናው በባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እንደሚጀምር የተገለጸ ሲሆን በቀጣይ በሌሎች ኮሌጆች እንደሚሰጥም ተመላክቷል።

የአማራ ክልል መንገድ ቢሮ ኀላፊ ጋሻው አወቀ (ዶ/ር) ሄልቬታስ ኢትዮጵያ በክልሉ ከሁለት ዓመታት በላይ ሥራ እየሠራ መቆየቱንም ገልጸው በእነዚህ ዓመታት 21 የሚደርሱ ተንጠልጣይ ድልድዮችን መሥራቱንም አስታውቀዋል።

በ2016 በጀት ዓመት 24 ተንጠልጣይ ድልድዮችን እየሠራ መኾኑንም ነው የተናገሩት ሃላፊው ድርጅቱ በአማራ ክልል እየሠራው ባለው ዘርፈ ብዙ ስራ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር እያደረገ መኾኑንም ገልጸዋል።

በሚቀጥለው ዓመት ከ84 በላይ ተንጠልጣይ ድልድዮችን እንደሚሰሩ የተናገሩት ሃላፊው ስራው በቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጆች መደገፉ ጥሩ አጋጣሚ መኾኑንም ተናግረዋል።

የተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታዎች በመሠረተ ልማት ተገልለው የቆዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በማገናኘት ግንኙነት እንዲፈጠር ያደርጋል፣ በተደጋጋሚ የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎችንም ይፈታል ተብሏል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

የሄሌቬታስ ኢትዮጵያ ተንጠልጣይ ድልድይ ፕሮጄክት ሥራ አሥኪያጅ ተስፋሁን ሞላ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በክልሉ የተንጠልጣይ ድልድይ ሲሠሩ መቆየታቸውን አስታውቀው አሁን ላይ ጥሩ የኾነ የተንጠልጣይ ድልድይ ልምድ እየተገኘ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በሄልቬታስ ኢትዮጵያ በተሠሩ 21 የተንጠልጣይ ድልድዮች ከ354 ሺህ በላይ ዜጎች ተጠቃሚ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። የተንጠልጣይ ድልድይ ግንባታ ቴክኖሎጂ በሥርዓተ ትምህርት ተካቶ በኮሌጆች መሰጠት በዘርፉ በቂ የሰው ኀይል እንዲፈጠር እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

በወቅታዊ የጸጥታ ሁኔታ፣ ኅብረተሰቡ በባለቤትነት ይዞ እንዲያሥተዳድር በማድረግ በኩል ችግሮች እየገጠሟቸው መኾኑንም ገልጸዋል።

የባሕርዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዲን ፈለቀ ውቤ ሥልጠናው የራሱ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆለት እንደሚሰጥም አስታውቀዋል። ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጁ ተንጠልጣይ ድልድዩን በበቂ ሁኔታ መሥራት እንደሚችልም አመላክተዋል። ሥልጠናው የኮሌጆችን አቅም እንደሚያሳድግም ገልጸዋል። መረጃውን ያገኘነው ከአሚኮ ነው።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button