ዜናማህበራዊ ጉዳይ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአዲሱ ዓመት የሰው ሕይወትን የሚቀጥፉ የመሳሪያ አፈ ሙዞች በሙሉ ወደ መጋዝን መግባት አለባቸው ሲሉ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 6/2015 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክተው ከሰሜን አሜሪካን ባስተላለፉት ያሳለፍነው አመት ችግሮች ወደ ቀጣይ አማት እንዳይሸጋገሩ በማድረግ አዲሱን አመት እንቀበል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ብጹእነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት በአዲሱ ዓመት የሰው ሕይወትን የሚቀጥፉ የመሳሪያ አፈ ሙዞች በሙሉ ወደ መጋዝን መግባት አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል።

ያለፈው ዓመት ያሳረፈብንን ሁለንተናዊ ተጽዕኖ በሚገባ አስተውለን፣ ዳግም ወደ አዲሱ ዓመት እንዳይሸጋገርብን ካላደረግን አዲሱ ዓመት ለኛ የሚሰጠን ትርጉም ምንድን ነው ሲሉ የጠየቁት ብጹእነታቸው ባለፉት ዓመታት በሃይማኖት፣ በባህል፣ በታሪክ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና ፖለቲካዊ እንዲሁም በሕዝባችን ሥር የሰደደውን የእርስ በርስ መጠራጠር ከልብ መርምረን ወደ ድሮው እኛነታችን ካልተመለከትንስ አዲስ ዘመን እያልን ማክበራችን ምን ፋይዳ የለውም ብለዋል።

ያለፈውን ጎጂ ነገር በመተው፤ ጠቃሚውን ግን ይበልጥ በማጠናከር አዲሱን ዓመት መቀበል አለብን ሲሉ አሳስበዋል።

በመለያየት፣ በመፎካከር፣ በመበቃቀል፣ በመናናቅ፣ የራስን ጥቅም ብቻ ለማስጠበቅ በመጣር፣ ጊዜ አገኘሁ ብሎ ኃይልን በመጠቀም፣ የሕዝብን ጥቅም ማስከበርና የሀገርን አንድነት ማስቀጠል አይቻልም ያሉት ብጹእነታቸው ሀገራችንንና ሕዝባችንን ወደ ዕመቀ ዕመቅ እየከተቱ ያሉ እንደዚህ ያሉ አስተሳሰቦች በመሆናቸው እነዚህ ሁሉ ከአሮጌው ዓመት ጋራ አብረው መወገድ አለባቸው ብለዋል።

ችግሮችን በውይይት፣ አሊያም በሕግ እየተፈቱ የሀገርና የሕዝብ ሉዓላዊነት ነጻነትና አንድነት መረጋገጥ አለበት ሲሉ ጠይቀዋል።

ሀገርንና ሕዝብን ለዘለቄታው በአንድነት የሚያስቀጥሉ የሕግ የበላይነትን ማክበር፣ እኩልነትን ማረጋገጥ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን እውን ማድረግ፣ የተጐዳውን መደገፍ፣ ሆድ የባሰውን ማለዘብ፣ የተጠቃውን ማጽናናት ሲቻል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በአዲሱ ዓመት ይህንን ለማድረግ በቊርጥ ከተነሣን ሰላማችን ወደነበረበት ይመለሳል ያሉት አቡነ ማትያስ በመልዕክታቸው፡ ሀገራችንም በበረከት ትሞላለች፤ ስለዚህም ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ ልጆቻችን ሁሉ ይህንን ጥሪያችንን ተቀብላችሁ የጥፋት መሳሪያችሁንም አስቀምጣችሁ ወደ ሰላም ማእድ ቀርባችሁ በክብ ጠረጴዛ በውይይት በመፍታት የሀገሪቱንና የሕዝቡን አንድነት እንድታስቀጥሉ ሁሉን በሚያይ እግዚአብሔር ስም እንማጸናችኋለን ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ በመጨረሻም አዲሱ ዓመት የሰላምና የፍቅር፣ የዕርቅና የይቅርታ የተፈናቀለው ወደቀየው የሚመለስበት፣ ሆድ የባሰው የሚጽናናበት፣ ፍትሕና ርትዕ የሚሰፍንበት የመሳሪያ ድምፅ የማይሰማበት ፍጹም የተግባቦት ዓመት እንዲሆን ምኞታቸውን ገልጸዋል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button