ዕለታዊፍሬዜናፖለቲካ

ዕለታዊ ዜና፡ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በመጪው ሳምንት የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ልየታ እንደሚጀምር ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ 

አዲስ አበባ፣ ጥር 5/2016፦ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች በመጪው ሳምንት የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ልየታ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽ አስታወቀ።

ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቶችን ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነፍጥ ያነሱ ወገኖች በሰላማዊ መንገድ ወደ ምክክሩ እንዲመጡ መንግስት ለሰላማዊ አማራጭ ቅድሚያ ሰጥቶ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ የበለጠ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።

ቀደም ብሎ የምክክር ኮሚሽኑን በተመለከተ በሩቅ ሆነው ቅሬታ ሲያነሱ የነበሩ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደነበሩ ገልጸዋል። አሁን ላይ ግን የኮሚሽኑን ትክክለኛ ተልዕኮ በቅርበት በመረዳት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለሀገራዊ ምክክር ስኬት በጋራ ለመስራት መግባባት ስለመፍጠራቸው አንስተዋል።

ለአብነትም በቅርቡ ከአፋር ህዝቦች ፓርቲ፣ ከሲዳማ ፌደራሊስት ፓርቲና ከኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ጋር የመግባቢያ ስምምነት ማዕቀፍ መፈረሙን ጠቅሰዋል።

ኮሚሽኑ እንደ ገለልተኛ ተቋም ከሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መስራት እንደሚፈልግ ገልጸው፣ ሁሉም ፓርቲዎች ወደ ምክክር እንዲገቡ መንግስት የበለጠ ማገዝ እንዳለበት አንስተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮሚሽኑ በሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ አፋር፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሀረሪ፣ አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተሞች የተሳታፊ ልየታ ማካሄዱን አስታውሰዋል።አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button