ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በሆሮ ጉዱሩ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ በሮ ቀበሌ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ስምንት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውንና ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ 

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16/ 2016 ዓ/ም፡_ በኦሮሚያ ክልል በሆሮ ጉዱሩ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ በሮ ቀበሌ ትላንት ታህሳስ 15 ቀን 2016 ዓ/ም በሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ስምንት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና ሶስት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት መደረሱን ነዋሪዎች ለአዲስ ስታንዳርድ ተናገሩ። 

ስሙ እንዲገለጽ ያልፈለግ አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪና አገልጋይ ለአዲስ ስታንዳርድ እንደገለጸው፣ ጥቃቱ የተፈጸመባቸው አማኞችን ጨምሮ የበሮ ሙሉውንጌል ቤተ ክርስቲያን አባሎች ከትላንት ጠዋት ጀምሮ በቤተክርስቲያኗ ቀጥር ግቢ ውስጥ የሚገኝ የበቆሎ ምርትን ለመሰብሰብ ቀጠሮ ተይዞ ነበር። 

በቀጠሮው መሰረትም በትላንትናው ዕለት ከጠዋት ጀምሮ በቁጥር በርከት ያሉ የቤተ ክርስቲያኗ አባላቶች የቦቆሎውን ምርት በመሰብሰብ ላይ እያሉ ድንገት በተፈጽመ የአየር ጥቃት ስምንት ሰዎች ወዲያው ሲሞቱ ሶስት ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት ደረሷል ሲል ገልጿል። 

በማከልም “ ጉዳት የደረሰባቸው ሶስቱ ሰዎች በአሁኑ ሰዓት ኮምቦልቻ ከተማ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው ነው፤ ነገር ግን በህይወት የመትረፍ እድላቸው እጅግ አነስተኛ ነው” በሏል።

የቤተክርስቲያኗ መሪ እንደገለጹት በድሮን ጥቃቱ ከተገደሉት ሰዎች መካከል የቤተ ክርስቲያኒቱ ኪቦርድ ተጫዋች የሆነው የ22 አመቱ ዳመነ ሊካ እና የ 21 አመቱ ዱጋሳ ዋቅኬኔ የተባሉ ውጣቶች ይገኙበታል። “ እነዚህ የተገደሉት ሰዎች የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች እና ሰላማዊ ሰዎች ነበሩ” ብሏል።

ሌላኛው አዲስ ስታንዳርድ ያነጋገረው የበሮ ቀበሌ ነዋሪ በሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመውን የድሮን ጥቃት እና በአማኞቹ ላይ የደረሰውን ግድያ በማረጋገጥ፤ በዛሬው ዕለት ከጠዋት ጀምሮ በወረዳው ውስጥ መንግስት “ሽኔ” እያል በሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች እና በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መካከል “ከባድ ውጊያ” እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል። 

አክሎም “ ዛሬ ጠዋት በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች እና በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች መካከል ከባድ ውጊያ እየተካሄደ በመሆኑ የሰውም ሆነ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ቆሟል። የቤተ ክርስቲያኗን አባላት ጨምሮ የባሮ ቀበሌ ነዋሪዎች የሟቾቹ የቀብር መርሃ ግብር ላይ መሳተፍ አልቻሉም” ብሏል። 

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ከዚህ ቀደም በዞኑ በተፈጸመ የደሮን ጥቃት ከ12 ሰዎች በላይ መገደላቸውንአዲስ ስታንዳርድ ነዋሪዎችን ዋቢ አደርጎ መዘገቡ ይታወሳል። መስከረም 26 ቀን  በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሃባቦ ጉዱሩ ወረዳ እራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት በሎ በሚጠራው ታጠቂ ሀይል እና በመንግስት ሀይሎች መካከል ሲካሄድ በነበረ ግጭት ላይ መንግስት በፈፀመው የድሮን ጥቃት 7  የወረዳው ነዋሪዎች ሞተዋል፡፡ በዚው ዞን በኮምቦልቻ ወረዳ  መስከረም 27 ቀን በተፈጸመው የአየር ጥቃት 5 ሰዎች ወድያው ሲሞቱ ሶስት ሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መደረሱን ነዋሪዎች ገልጸዋል። በተጨማሪም በእለቱ ረፋድ 4፡30 ላይ የመንግስት ሀይሎች በወረዳው በሚገኘው ሁላ ጉቶ ቀበሌ ውስጥ በከፈቱት ተኩስ ሁለት ወጣቶች እና አንድ አዛውንት ተገድለዋል፡፡አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button