ዜናማህበራዊ ጉዳይህግ እና ፍትህ

ዜና፡ ኢሰመጉ መንግስት በሀገሪቱ በውጭ ዜጎች ላይ ጭምር በመፈጸም ላይ ባለው የሰዎች እገታ በቂ ትኩረት እንዲሰጥ ጠየቀ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም፡- በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የውጭ ሀገር ዜጎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ላይ በታጠቁ ቡድኖች እየተፈጸመ ያለው እገታ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ መምጣቱን እና ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰትን እያስከተለ እንደሚገኝ ኢሰመጉ ጥቅምት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታወቀ።

መንግስት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ አይደለም ሲል የተቸው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ ዜጎች በሚታገቱበት ወቅት ባገታቸው አካል የመብት ጥሰት፣ ጭካኔ የተሞላበት አዋራጅ አያያዝ ወይም ቅጣት እየደረሰባቸው መሆኑን የደረሰው መረጃ ማመላከቱን በመግለጫው አካቷል።

በሀገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣው እገታ ዜጎች ላይ ደህንነት እንዳይሰማቸው ያደረገ በመሆኑ በነጻነት ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የዕለት ተዕለት ተግባራቸውን ለማከናወን መቸገራቸውን እና ኑሯቸው ስጋት የተሞላ እንዲሆን ማድረጉን ጠቁሟል።

የእገታ ድርጊት የሚፈጸምባቸው አካባቢዎች በተደጋጋሚ ጊዜ የሚፈጸምባቸው ቦታዎች መሆናቸውም ይታወቃል ያለው ኢሰመጉ ዘላቂ መፍትሔ ባለመሰጠቱ በአካባቢዎቹ የሚኖሩ ሰዎች የእገታ ሰለባ መሆናቸውን እና ቁጥራቸው አነስተኛ የማይባሉ ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውቋል።

ተመሳሳይ እገታዎች በኦሮሚያ ክልል ሰሜን እና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ መፈጸማቸውን የጠቆመው ኢሰመጉ በእገታዎች የውጪ ሀገር ዜጎችም ሰለባ መሆናቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንደደረሱት አመላክቷል።

ኢሰመጉ ባሰተላለፈው ጥሪ የፌደራል መንግስት እየተፈጸሙ ላሉ የእገታ ድርጊቶች በቂ ትኩረት እንዲሰጥ እና ፈጻሚዎችን ተጠያቂ እንዲያደርግ ጠይቋል። የፌደራል መንግስቱ ሰዎችን አስገድዶ ከመሰወር ለመጠበቅ የወጡ አለም አቀፍ ስምምነቶችን እንዲያጸድቅም ጠይቋል።

የኦሮምያ ክልል መንግስት በክልሉ በታጣቂ ቡድኖች እየተፈጸመ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማውገዝና አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ወንጀለኞችን ለህግ እንዲያቀርብ የጠየቀው ኢሰመጉ የኦሮሚያ ክልል መንግስት እንዲሁም የፌደራል መንግስት የጸጥታ አካላት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ውስጥ የሚፈጸሙ እገታዎችን እንዲያስቆም እንዲሁም ታግተው የሚገኙ ዜጎችን ተገቢውን የህግ ስነ ስርዓት በመከተል እንዲያስለቅቅ አሳስቧል።

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ኢሰመጉ ተጨማሪ የምርመራ ስራዎችን በመስራት ዝርዝር ዘገባ እንደሚያዘጋጅ ጠቁሟል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button