ዜናፖለቲካ
በመታየት ላይ ያለ

ዜና፡ በአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች እየተከናወኑ ባሉ ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች ንፁሀን ዜጎች ሰለባ እየሆኑ ነው – ኢዜማ

አዲስ አበባ፣ ጥር 16/2016 ዓ.ም፡- የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ – ኢዜማ ዛሬ ጥር 16 ቀን 2016 የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ጉዳይ በተመለከተ፣ የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይዞታ ዙሪያ፣ በትግራይ ክልል የተከሰተው ድርቅና ረሀብን በተመለከተ እና በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የቀጠለው ጦርነት በተመለከተ በጽ/ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ኢዜማ በሰጠው መግለጫ በአማራ እና ኦሮምያ ክልሎች መንግስት በሚወስዳቸው እርመጃዎች በተለይም በድሮን የሚደረጉ የአየር ላይ ጥቃቶች ንፁሀን በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ ጉዳት እያደረሱ መሆኑን ከዓይን እማኞች የሰበሰብኩት መረጃ የሳያል ብሏል።

በክልሎቹ ከመንግሥት ጋር የሚፋለሙ ታጣቂዎችም “ከተሞችን እንቆጣጠራለን” በሚል በሚያደርጉት የከተማ ውስጥ ውጊያ በሰው ሕይወትና ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ክልሎች ባለው “ጦርነት” ምክንያት የግብርና ሥራዎች ተስተጓጉለዋል፣ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በአግባቡ መከታተል አልቻሉም፣ ዜጎች ለችግር ተጋልጠዋል፣ የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ደረጃ ተዳክመዋል፣ መሠረተ ልማቶችም ወድመዋል ሲል ገልጿል፡፡

ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ከዚህም የባሱ ለሀገር ህልውና አስጊ የሆኑ ቀውሶች መፈጠራቸው የሚቀር አይመስልም ያለው ኢዜማ በእነዚህ ጦርነቶች እንደሀገር ሁላችንም ከስረናል፤ ያተረፈም ካለ ኢትዮጵያን በዓይነ ቁራኛ የሚከታተሉ ጠላቶቿ ብቻ ናቸው ብሏል።

የሚከፈል የትኛውም አይነት ዋጋ ካለ ለሰላም ሲባል ለመክፈል ቁርጠኛ በመሆን ማህበረሰቡ ከተዘፈቀበት እንግልት ስቃይና ስጋት የተሞላ ህይወት እፎይ እንዲል ማድረግን ቅድሚያ ልትሰጡት ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡

የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ጉዳይ በተመለከተ በሰጠው መግለጫ መንግሥት ሰላምና ደኅንነትን በማስከበር ረገድ ከፍተኛ ድክመት እንዳለበት መተማመን ያስፈልጋል ሲል ገልጾ ሹፌሮች፣ ነጋዴዎች፣ ገበሬዎች፣ የግልና የመንግሥት ሠራተኞች፣ ተማሪዎች፣ ጉዳይ አስፈጻሚዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ የሃይማኖት ተጓዦች ሁሉ ከመኖሪያቸው አጭር ኪሎሜትሮችን ሳይቀር ወጥተው መግባት ሲሳናቸው እየተመለከትን ነው ብሏል፡፡

Download the First Edition of Our Quarterly Journal

ዘውግ ላይ የተንጠለጠለው ፖለቲካችን ለሰላም እጦታችን በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ እንደሆነ እሙን ነው ያለው ኢዜማ ከመንግሥት ድክመት በተጨማሪ ለዜጎች ሰላምና ደኅንነት ማጣት ከመንግሥት ውጭ ያሉ ኃይሎችም የማይናቅ ሚና እንዳላቸው በቅጡ እንረዳለን ሲል ጠቁሟል።

የሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ይዞታ በተመለከተ በሰጠው መግለጫ በመንግሥት በኩል መደበኛ አሠራር መስሎ የቀጠለው ሕገወጥ የጅምላ እስርና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል ብሏል፤ ተለይም ላለፉት ጥቂት ሳምንታት በአዲስ አበባ ዙሪያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጅምላ ታፍሰው በየእስር ቤቱ ሲጋዙ ነበር ሲል በአብነት ጠቅሷል፡፡

በትግራይ ክልል የተከሰተው ድርቅና ረሀብን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ የተከሰተውን ችግሩ እውቅና ሰጥቶ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ጉዳዩን ቁጥሮች ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ በማድረግ ከክልሉ አስተዳደር ጋር እሰጣ እገባ ጀምሯል ሲል ተችቷል፡፡

ጉዳዩን የቁጥር ጨዋታና የፖለቲካ ትርፍ ማግኛ ከማድረግ ይልቅ ለረሀብ አደጋና ለሞት የተጋለጡ ዜጎችን ለመታደግ አስቸኳይ ሀገርአቀፍ ርብርብ ሊደረግ ይገባል ሲል አሳስቧል፡፡ አስ

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button