ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ በፌስቡክ በተከናወነ ዘመቻ ወደ ሳዑዲ አረብያ በማቅናት በቤት ሰራተኝነት በኤጀንሲዎች አማካኝነት ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ግፍ እየተፈጸመባቸው ነው ተባለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 5/2016 .ም፡ በኢትዮጵያ በመንግስት እውቅና ተችሮት በፌስቡክ በተካሄደ ዘመቻ ወደ ሳዑዲ አረብያ የቤት ሰራተኞች ቅጥር መፈጸሙ ለህገወጥ አዘዋዋሪዎች፣ የጉልበት ብዝበዛ ፈጻሚዎች ግፍ ለመፈጸም የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሮላቸዋል ሲል ግሎብ ኤንድ ሜይል ድረገጽ ባሰራጨው ዘገባ አስታውቋል።

በቤት ሰራተኛ መልማይ ኤጀንሲ ቅጥር ፈጽማ ወደ ሳዑዲ አረብያ በመጓዝ በስራ ላይ የነበረች ፍቅርተ የተባለች ኢትዮጵያዊት ታሪክን በአብነት ያስነበበው ድረገጹ ከአዲስ አበባ ወደ ሳዑዲ አረብያ ያቀናቸው ፍቅርተ አሰሪዎቿ ምንም አይነት ምግብ ሳይሰጧት በረሃብ በርካታ ሳምንታት አድካሚ ስራ ሲያሰሯት ከቆዩ በኋላ ምንም አይነት ክፍያ ሳይፈጽሙላት ደካማ ናት ብለው ለኤጀንሲው እንደመለሷት አስታውቋል።

ፍቅርተ መንግስት 500ሺ የቤት ሰራተኞችን ወደ ሳዑዲ አረብያ ለመላክ መስማማቱን መግለጹ እና ይህም በመንግስት መገናኛ ብዙሃን መነገሩ እምነት አሳድሮባት በቀጣሪ ኤጀንሲዎች በኩል መሄዷን ድረገጹ አስብቧል።

ጉዳዩን አስመልክቶ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተቋማት መንግስትን በመተቸት በወቅቱ መግለጫ አውጥተው እንደነበር ያወሳው ግሎብ ኤንድ ሜይል በአረብ ሰላጤው ሀገራት በየአመቱ 10ሺ የሚደርሱ ከደቡብ ኤሲያ የሚመጡ ሰራተኞች እንደሚሞቱ ጥናት መጠቆሙን በአብነት አስቀምጧል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያለበት የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን ችላ በማለት ያለበትን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ ሲል ፕሮግራሙን ከማስተካከል ይልቅ ቀጥሎበታል ሲል ድረገጹ በዘገባው ተችቷል።

እንደ ፍቅርተ አይነት ኢትዮጵያውያንን ለመማረክ ሲል መንግስት በተቋማቱ የፌስቡክ ገጽ ጭምር ፕሮግራሙን በዘመቻ እንዲተዋወቅ ማድረጉን የጠቆመው ግሎብ ኤንድ ሜይል ድረገጽ የቤት ሰራተኞችን ለመመልመል በተካሄደው ዘመቻ ካሳለፍነው አመት 2015 የካቲት ወር ወዲህ ብቻ 200 የሚሆኑ የመንግስት ተቋማት በፌስቡክ ገጾቻቸው ፕሮግራሙን በዘመቻ ማስተዋወቃቸውን ያሰባሰበው መረጃ እንደሚያመላክት አስታውቋል።

ፕሮግራሙ በየወረዳው ባሉ የገዢው ፓርቲ ቅርንጫፎች ጭምር በዘመቻ በፌስቡክ ገጾቻቸው መተዋወቁን ዘገባው አመላክቷል። በእነዚህ የፌስቡክ ገጾች የተላለፉት መልዕክቶች ወደ ሳዑዲ አረብያ የሚጓዙ ኢትዮጵያውያን በሳዑዲ በሚኖራቸው ቆይታ የሀገሪቱ መንግስት የሰራተኛ እና አሰሪ ህግ እንደማያስከብርላቸው ይልቁንም ከፈላ በሚባል ዘዴ እንደ ድረገጹ አገላለጽ ዘመናዊ የባርነት ዘዴ የእስፖንሰር አካሄድ ብቻ እንደሚጠበቁ አልተገለጸላቸውም ሲል ተችቷል። አስ

Download the First Edition of Our Quarterly Journal
ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button