ዜናማህበራዊ ጉዳይ

ዜና፡ በኢትዮጵያ በየአመቱ ከሚመዘገቡ 77 ሺ የካንሠር ህሙማን መካከል ሕክምና የሚያገኙት 12 ሺህ ገደማ መሆናቸው ተጠቆመ

አዲስ አበባ፣ ጥር 20/2016 ዓ.ም፡- በኢትዮጵያ በየአመቱ ከሚመዘገበው 77 ሺህ የሚጠጋ የካንሠር ህሙማን 12 ሺህ ያህሉ ብቻ ሕክምናውን እንደሚያገኙ የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

በ24 የመንግሥት ሆስፒታሎች የመድኃኒት ሕክምና (ኬሞቴራፒ) እየተሰጠ መሆኑን በሚኒስቴሩ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ስራ አስፈፃሚ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የአዕምሮ ጤና ዴስክ መሪ ዶ/ር ሰላማዊት አየለ መግለጻቸውን የፋና ዘገባ ያመላክታል።

ሁለንተናዊ የካንሠር ሕክምና አገልግሎት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል፣ በሐዋሳ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፣ በአይደር ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና በሐሮማያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እየተሰጠ መሆኑን ሃላፊዋ መናገራቸውን ዘገባው አስታውቋል።

የሕክምናውን ተደራሽነት ለማስፋት እየተሠራ መሆኑን በመግለጽ በ30 ሚሊየን ዶላር ወጪ የካንሠር ሕክምና ማዕከላት ማስፋፊያ በጥቁር አንበሳ፣ ጅማ፣ ሐሮማያ፣ ሐዋሳና ጎንደር እየተከናወነ ነው ማለታቸውንም አካቷል።

ወደ ሕክምና ከሚመጡት 75 በመቶዎቹ ህመሙ ውስብስብ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ይመጣሉ፤ ይህም የታማሚውን ታክሞ የመዳን ዕድል ይቀንሰዋል፤ ሕክምናውንም የበለጠ ውድ ያደርገዋል ሲሉ ማሳሰባቸውን ዘገባው አመላክቷል።

ተጨማሪ አሳይ

ተዛማጅ ጽሑፎች

Back to top button